የሀማስ መሪ ሀኒየህ ስርአተ ቀብሩ ኳታር ውስጥ ሊፈጸም ነው
ሀኒየህ፣ በእስራኤል እና ሀማስ መካከል ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ በሀማስ መሪዎች ላይ ከተፈጸሙት ተከታታይ ጥቃቶች ውስጥ በአንዱ ሰለባ ሆነዋል
ሀማስ እና እስራኤል ለግድያው እስራኤልን ተጠያቂ ያደረጉ ሲሆን የበቀል እርምጃ እንደሚወስዱም ዝተዋል
የሀማስ መሪ ሀኒየህ ስርአተ ቀብሩ ኳታር ውስጥ ሊፈጸም ነው።
ባለፈው ሀሙስ እለት በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን ውስጥ የተገደለው የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማስ ዋና የፖለቲካ መሪ እስማኤል ሀኒየህ ስርአተ ቀብሩ ኳታር ውስጥ እንደሚፈጸም ተገልጿል።
ሀኒየህ፣ በእስራኤል እና ሀማስ መካከል ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ በሀማስ መሪዎች ላይ ከተፈጸሙት ተከታታይ ጥቃቶች ውስጥ በአንዱ ሰለባ ሆኗል።
የሀኒየህ አስከሬን የጸሎት ስነ ስርአት ከተካሄደ በኋላ ከኳታር ዋና ከተማ ዶሃ በስተሰሜን በኩል በሚገኘው ሉዛ መካነመቃብር ያርፋል ተብሏል።
የሀማስ የፖለቲካ ቢሮ አባል የሆኑት ኢዛት አል-ሪሽቅ ሰዎች በመላው አለም በሚገኙ መስጊዶች ለነፍሱ እንዲጸልዩለት ጥሪ አቅርበዋል።
አል-ሪሺቅ ባወጡት መግለጫ "ዛሬ አርብ፣ የግድያ ወንጀልን እና በጋዛ ሰርጥ እየተካሄደ ያለውን የዘርማጥፋት ተግባር የምናወግዝበት ይሁን" ብለዋል።
የሀማስ ከፍተኛ ባለስልጣን ካሊል አል-ሀያ ከሀኒየህ ጋር አብረው የነበሩትን የአይን እማኞች ጠቅሰው እንደናገሩት፣ ሀኒየህ የተገደለው ቴህራን ውስጥ ያረፈበት የእንግዳ ማረፊያ በቀጥታ በሚሳይል በመመታቱ ነው።
ሀማስ እና እስራኤል ለግድያው እስራኤልን ተጠያቂ ያደረጉ ሲሆን የበቀል እርምጃ እንደሚወስዱም ዝተዋል። እስራኤል ግን ለግድያው ኃላፊት አልወሰደችም፤ ማስተባበያም አልሰጠችም።
ይህ ጥቃት በርካታ የሀማስን እና የሊባኖሱን ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላን ከፍተኛ መሪዎች ከገደሉት ውስጥ አንዱ ሲሆን በጋዛ በሀማስ እና እስራኤል መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት ከቀይ ባህር እስከ ሊባኖስ-እስራኤል ድንበር እና ባሻገር በመለጠጥ ቀጣናዊ እንዲሆን ሊያደርገው ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን የሀኒየህ ግድያ 10 ወራት ያስቆጠሰውን ጦርነት በተኩስ አቁም ለመቋጨት የሚደረገውን አለምአቀፍ ጥረት ይጎዳል ብለዋል።
ግድያው ወደ ተኩስ አቁም የመድረስ እድልን ይጎዳ እንደሆነ በትናንትናው እለት የተጠየቁት ባይደን "አይጠቅምም" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ኳታር የሀማስ ዋና መቀመጫ ሀገር ነች።
ኳታር ከግብጽ እና ከእስራኤል ዋነኛ አጋር ከአሜሪካ ጋር በመሆን የማደራደር ጥረቱን ስትመራ ቆይታለች። ሀኒየህ የጋዛ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ በተካሄዱ ቀጥተኛ ያልሆኑ የተኩስ አቁም ንግግሮች የሀማስ የአለምአቀፍ ዲፕሎማሲ ፊት ሆኖ ሲያገለግል መቆየቱ ይታወሳል።