እስራኤል ለወራት ባደረገችው ሚስጢራዊ ዝግጅት ሀኒየህ በተኛበት ክፍል ውስጥ መገደሉ ተገልጿል
የሐማስ የፖለቲካ ሃላፊ እስማኤል ሀኒየህ ግድያ እንዴት ተፈጸመ?
ከ10 ወራት በፊት የተጀመረው የእስራኤል- ሐማስ ጦርነት አሁንም እንደቀጠለ ሲሆን የእስራኤል ጦር የሐማስ አመራሮችን በፍልስጤም እና በሌሎች ሀገራት ኢላማ አድርጓል፡፡
የሐማስ የፖለቲካ ቢሮ ሀላፊ እስማኤል ሀኒየህ በኢራን መዲና ቴህራን በተፈጸመባቸው ጥቃት መገደላቸው ይታወሳል፡፡
ሀኒየህ በእስራኤል ተገድሏል ከመባሉ ውጪ ግድያው እንዴት እንደተፈጸመ ሳይገለጽ ቆይቷል፡፡
ኒዮርክ ታየምስ የኢራን፣ አሜሪካ እና እስራኤል ከፍተኛ ባለስልጣናትን ዋቢ አድረጎ እንደዘገበው ከሆነ እስራኤል የሀኒየህን ግድያ ለመፈጸም ለወራ ስትዘጋጅ ከርማለች፡፡
የሃማስ የፖለቲካ መሪ ኢስማኤል ሀኒየህ ሶስት ልጆች ተገደሉ
ሀኒየህ ወደ ኢራን በሚጓዝበት ወቅት በሀገሪቱ ከፍተኛ ወታደራዊ ጥበቃ በሚደረግበት አንድ አፓርታማ ላይ ብቻ ያርፍ እንደነበር ተገልጿል፡፡
የእስራኤል ስለላ ድርጅት ሞሳድ በሚስጥር ባደረገው ክትትል ይህን ከተረዳ በኋላ ወደ ሀኒየህ መኝታ ቤት ቦምብ እንዲገባ መደረጉን በዘገባው ለይ ተጠቅሷል፡፡
እንደ ዘገባው ከሆነ ሀኒየህ አዲሱ የኢራን ፕሬዝዳንት በዓለ ሲመት ለመታደም በሚል ወደ ቴህራን ያመራ ሲሆን ዝግጅቱ ተጠናቆ ለእረፍት ወደ ክፍሉ ከገባ በኋላ በተኛበት ተገድሏል፡፡
እስራኤል ሀኒየህን እና ጠባቂውን ከትናንት በስቲያ ረቡዕ ምሽት ላይ ከርቀት ማፈንዳት በሚቻል ቦምብ አማካኝነት ግድያውን እንደፈጸመች ተገልጿል፡፡
ግድያው የተፈጸመበት ቦምብም ከሁለት ወራት በፊት ወደ ስፍራው እንዲገባ የተደረገ እንደሆነም በዘገባው ላይ ተገልጿል፡፡
የኢራን ወታደራዊ እና የደህንነት ባለስልጣናት የግድያው የተፈጸመበት ወቅት ጥብቅ ጥበቃ በሚደረግበት ወቅት መሆኑ ከመቼውም ጊዜ በላይ አበሳጭቷቸዋል ተብሏል፡፡
እስራኤል በይፋ ግድያውን ስለመፈጸሟ እስካሁን ያልተናገረች ሲሆን ወዳጅ ለሚባሉ ምዕራባዊያን ሀገራት ግድያውን ስለመፈጸሟ ማብራሪያ እንደሰጠች ተገልጿል፡፡
እስማኤል ሀኒየህ በሐማስ እና እስራኤል መካከል በሚደረጉ ድርድሮች ላይ ዋነኛ ተሳታፊ የነበረ ሲሆን የግድያው መፈጸም በርካታ ሀገራትን አስቆጥቷል፡፡
አሜሪካ በሀኒየህ ግድያ ዙሪያ እውቅና እና ተሳትፎ እንደሌላት የገለጸች ሲሆን ኢራን በበኩሏ እስራኤልን እንደምትበቀል ዝታለች፡፡