የሃማስ የፖለቲካ መሪ ኢስማኤል ሀኒየህ ሶስት ልጆች ተገደሉ
ሀኒየህ በሰሜናዊ ጋዛ ለኢድ ዘመዶቻቸውን ለመጠየቅ የወጡ ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው በእስራኤል ጥቃት መገደላቸውን ተናግረዋል
እስራኤል ለሃማስ መሪ ልጆች ግድያ እስካሁን ሃላፊነቱን አልወሰደችም
የሃማስ የፖለቲካ መሪ ኢስማኤል ሃኒየህ ሶስት ልጆች ተገደሉ።
ሃኒየህ በጋዛው ጦርነት ቆስለው በኳታር መዲና ዶሃ ህክምና እየተደረገላቸው የሚገኙ ፍልስጤማውያንን ሲጎበኙ ነው መርዶውን የሰሙት።
ሃዘም፣ አሚር እና ሞሀመድ የተባሉት ልጆቻቸው በእስራኤል ጥቃት መገደላቸውን ያረጋገጡት የሃማስ መሪው ሃኒየህ፥ ቁጥራቸውን ያልጠቀሷቸው የልጅ ልጆቻቸውም ህይወታቸው ማለፉን ተናግረዋል።
የሃኒየህ ልጆች የተገደሉት በሰሜናዊ ጋዛ ሻቲ የስደተኞች ጣቢያ ለሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ለኢድ አልፈጥር በዓል መልካም ምኞታቸውን ለመግለጽ በመውጣታቸው ነው።
ሶስት ልጆችና የልጅ ልጆቻቸውን ያጡት ሃኒየህ “እስራኤል በበቀል፣ ግድያና ደም መፍሰስ ታውራ በጋዛ ከአለም ህግ ውጪ የዘር ጭፍጨፋ እየፈጸመች ነው” ብለዋል።
“የልጆቼ ደም ከህዝባችን የተለየ አይደለም፤ እስራኤል ልጆቼን በመግደል ሃማስ አቋሙን ይለውጣል የሚል የቅዠት ሀሳብ አስባ ይሆናል ግን ይሄ በፍጹም አይሆንም” ማለታቸውንም ሬውተርስ ዘግቧል።
ግድያው በተኩስ አቁም ድርድሩ ሃማስ ያቀረባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች እንደማያስለውጠው በመጥቀስም “መስዋዕትነት በሚከፍሉና በሚቆስሉ ወገኖቻችን ነጻነታችን እናውጃለን” ብለዋል።
ሃማስና መሪዎቹን በሽብርተኝነት የፈረጀችው እስራኤል እስካሁን ስለሃኒየህ ልጆችና የልጅ ልጆች ግድያ አስተያየት አልሰጠችም።
በ2017 የሃማስ የፖለቲካ መሪ ሆነው የተሾሙት ኢስማኤል ሃኒየህ እስራኤል አጥብቃ ከምትፈልጋቸው የቡድኑ መሪዎች ተጠቃሽ ናቸው።
በኳታር መዲና ዶሃ የሚኖሩት ሃኒየህ ወደ ግብጽ ደጋግመው በማምራት የሃማስን የተኩስ አቁም ምክረሃሳብ ማቅረባቸው ይታወሳል።