እስራኤል የሀሰን ናስራላህ ተተኪ ይሆናሉ በተባሉት ሀሺም ሼፌዲን መኖሪያ ቤት ቤት ላይ ጥቃት ፈጸመች
አዲሱ የሂዝቦላህ መሪ ይሆናሉ የተባሉት ሰው እስካሁን ስለመገደላቸው አልተረጋገጠም
እስራኤል ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ባደረሰቻቸው ጥቃቶች 37 ንጹኃን ሲገደሉ ከ150 በላይ ቆስለዋል
እስራኤል የሀሰን ናስራላህ ተተኪ ይሆናሉ በተባሉት ሀሺም ሼፌዲን መኖሪያ ቤት ቤት ላይ ጥቃት ፈጸመች፡፡
እስራኤል ከአንድ ሳምንት በፊት በቤሩት በፈጸመችው ጥቃት የሊብኖሱ ሄዝቦላህ መሪ ሼክ ሀሰን ናስራላህን መግደሏ ይታወሳል።
ይህን ተከትሎ የሂዝቦላህ ቀጣይ መሪ የነብዩ መሀመድ የዘር ሀረግ አላቸው የሚባሉት ሀሺም ሴፌዲን የሀሰን ናስራላህ ተተኪ እንደሚሆኑ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡
የእስራኤል አየር ሀይል ዛሬ ጠዋት ላይ ሀሺም ሰፌዲን አሉበት በተባለ ስፍራ ላይ የአየር ድብደባ ፈጽሟል፡፡
ከቤሩት ኤርፖርት አጠገብ ይገኛል የተባለው ይህ ሀሺም ሰፌዲን አሉበት የተባለው ስፍራ የእስራኤል ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች ተደጋጋሚ እና ከባድ ድብደባ እንዳደረጉ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ይሁንና ሂዝቦላህም ሆነ እስራኤል እስካሁን ሀሺም ሰፌዲን በጥቃቱ ኢላማ ስለመሆናቸው እና ስለመገደላቸው ያሉት ነገር የለም፡፡
ሀሺም ሰፌዲን ከናስራላህ የባሰ ደመ ሞቃት ናቸው የተባለ ሲሆን በእስራኤል ጥቃት የተገደሉ ወታደራዊ አዛዦችን ምትክ በማስመረጥ ሂዝቦላህን ወደ ቀድሞ አቋሙ ሊመልሱ እንደሚችሉ ከሰሞኑ ሲገለጽ ነበር።
ለእስራኤል የከረረ ጥላቻ አላቸው የሚባሉት ሀሺም የሂዝቦላህ ፖለቲካ ክንፍን ሲመሩ ቆይተዋል።
የሀሰን ነስራላህ አጎት ናቸው የሚባሉት ሀሺም በፈረንጆቹ 2017 ላይ በአሜሪካ እና ሳውዲ አረቢያ በአሸባሪነት ተፈርጀዋል።
እስራኤል በሊባኖስ የተለያዩ አካባቢዎች የአየር ላይ ጥቃቶችን የቀጠለች ሲሆን ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ብቻ 37 ንጹሃን ሲገደሉ ከ150 በላይ ደግሞ መቁሰላቸውን የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡