የእስራኤል ጦር በደቡባዊ ሊባኖስ በከፈተው የምድር ውግያ ወደ ፊት እየገፋ መሆኑ ተገለጸ
የእግረኛ ጦሩ የሄዝቦላህ ዋሻዎችን ፣ ወታደራዊ መሰረተ ልማቶችን እና ሌሎች ኢላማዎችን ማጥቃት ላይ ትኩረት አደርጋለሁ ብሏል
እስራኤል በሊባኖስ በእግረኛ ጦር በከፈችው ጥቃት ከሄዝቦላህ ታጣቂዎች ጋር ውግያ ላይ ትገኛለች
የእስራል ጦር በደቡባዊ ሊባኖስ በጀመረው የምድር ውግያ ከሄዝቦላህ ታጣቂዎች ጋር እየተፋለመ እንደሚገኝ ተነግሯል፡፡
አስራኤል ድንበሩን አቋርጣ ከገባች በኋላ ሁለቱ አካላት የፊት ለፊት ውግያ ሲያደርጉ ይህ ለመጀመርያ ጊዜ መሆኑን ሮይተርስ አስነብቧል፡፡
የእስራኤል ጦር ይፋ ባደረገው መረጃ በድንበር አቅራቢያ በተጀመረው ዘመቻ የመካናይዝድ ብርጌድ እና የእግረኛ ጦር እየተሳተፉ እንደሚገኙ ገልጿል፡፡
ማሩውን ኤል ሩስ በተባለች የድንበር ከተማ ከእስራኤል ጦር ጋር ውግያ ውስጥ እንደሚገኝ ያስታወቀው ሄዝቦላህ በበኩሉ፤ አንድ የእስራኤል ወታደራዊ አዛዥ መግደሉን በተጨማሪም በድንበር አቅራቢያ በሚገኙ ወታደራዊ ማዘዣ ጣብያዎች ላይ የሮኬት ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል፡፡
የቡድኑ የሚዲያ ዋና ሃላፊ ሞሀመድ አፊፍ ሄዝቦላህ ቴልአቪቭ የከፈተችውን የምድር ውግያ መቀልበስ የሚያስችል በቂ የሰው ሀያል ፣ ተተኳሽ እና የጦር መሳርያ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
ጦሩ ከሌባኖስ ሉአላዊ ግዛት ሙሉ ለሙሉ እስኪወጣ ድረስ ትግላችንን እንቀጥላለን ያሉ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በድንበር ከተሞች ላይ ውግያ እየተደረገ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል፡፡
ከሊባኖስ ጋር በሚያዋስናት ሰሜናው ድንበር አቅራቢያ ተጨማሪ ሀይል እያሰፈረች የምትገኘው እስራኤል ከ36ተኛው ክፍለ ጦር ውስጥ የሚገኙ የጎላን ብርጌድ ፣ 6ተኛው የእግረኛ ጦር እና 188ተኛው ሜካናይዝድ ጦር ወደ ሊባኖስ ለመግባት በተጠንቀቅ ላይ ይገኛሉ ብላለች፡፡
በተጨማሪም ከሰሞኑ የሀገሪቱ ኮማንዶ ከፈጸማቸው አሰሳ እና ዘመቻዎች ተሻግሮ ውግያው ወደ ሙሉ ወታደራዊ ግጭት ሊያድግ እንደሚችል ነው ያስታወቀችው፡፡
ምንም እንኳን ጦርነቱ ሊስፋፋ የሚችልበት እድል እንዳለ የእስራኤል ጦር ቢያሳውቅም ዋና ከተማዋን ቤሩት ጨምሮ በደቡባዊ ሊባኖስ በሚገኙ በትላልቅ ከተሞች ላይ ውግያ የማድረግ እቅድ እንደሌለው ተናግሯል፡፡
ይልቁንም የእግረኛ ጦሩ የሄዝቦላ ዋሻዎችን ፣ ወታደራዊ መሰረተ ልማቶችን እና ሌሎች ኢላማዎችን ማጥቃት ላይ ትኩረት አደርጋለሁ ነው ያለው፡፡
አለም አቀፉ ማህበረሰብ ፣ የተባበሩት መንግስታት እና አሜሪካ በቀጠናው እያየለ የመጣው ውጥረት እንዲረግብ ተደጋጋሚ ጥሪ ቢያቀርቡም አሁንም ግጭቱ በፍጥነት እየተጓዘ ይገኛል፡፡
ዛሬ ማለዳ በዋና ከተማዋ ቤሩት ደቡባዊ ክፍል የሄዝቦላህ ጠንካራ ይዞታ ናቸው በተባሉ ስፍራዎች ላይ የአየር ጥቃቷን ያስቀጠለችው እስራኤል በቀጠናው በኢራን የሚደገፉ ቡድኖች በሚገኙባቸው ሀገራትንም እንደምታጠቃ ዝታለች፡፡
እንደ ሊባኖስ ጤና ሚንስቴር መረጃ አንድ ሳምንት በተሻገረው የእስራኤል ጥቃት እስካሁን ከ1900 በላይ ሰዎች ሲገደሉ ከ9ሺህ የሚሻገሩት ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡