እስራኤል በኢራን የምትሰጠው የአጸፋ ምላሽ የኒውክሌር ጣብያዎችን ኢላማ ታደርግ ይሆን?
አሜሪካ በኒውክለር ጣብያዎቹ ላይ የሚደርስን ጥቃት እንደማትደግፍ አስታውቃለች
ጆ ባይደን የአጸፋ ምላሹ የተመጣጠነ ሊሆን እንደሚገባው አሳስበዋል
ኢራን በእስራኤል ላይ በባለስቲክ ሚሳኤሎች ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ ከፍተኛ የአጸፋ ምላሽ ከኔታንያሁ አስተዳደር እንደሚጠብቃት እየተነገረ ይገኛል።
ወታደራዊ ማዛዣዎችን እና ካምፖችን ኢላማ እድርጓል በተባለው የማክሰኞው የተሄራን ጥቃት በቀጠናው እያየለ የሚገኝውን ውጥረት ከፍ ወዳለ ደረጃ እያሸጋገረው እንደሚገኝ እየተዘገበ ይገኛል።
ቴልአቪቭ ከኢራን ለደረሰባት ጥቃት በቅርቡ ምላሹን እንደምትሰጥ እየተጠበቀ ሲሆን ከነዚህ የጥቃት ኢላማዎች መካከል የኢራን የኒውክሌር ማብላያ ጣብያዎች ቀዳሚ ሊሆኑ እንደሚችል ተገምቷል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የመካከለኛው ምስራቅ አጋራቸው እስራኤል የኒውክሌር ጣብያዎችን ማጥቃቷን አንደግፍም ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ በትናንትናው እለት በቀጠናው ሁኔታ ዙርያ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ የቡድን 7 አባል ሀገራት ሁላችንም እስራኤል የአጸፋ ምላሽ የመስጠት መብት እንዳላት ተስማምተናል ነገር ግን ጥቃቱ የተመጣጠነ መሆን አለበት ነው ያሉት።
በተጨማሪም በቴሄራን ላይ አዲስ ማዕቀብ እንደሚጣል የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ በአጻፋ ምላሹ ዙርያ ከጠቅላይ ሚንስትር ኔታንያሁ እና ከሌሎች አካላት ጋር በቅርበት እየተነጋገሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
አንዳንድ ተንታኞች ዋሽንግተን ቀጠናዊ ግጭትን ለማስቀረት በእስራኤል የአጸፋ ምላሽ መጠን ዙርያ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን ማድረግ እንደሚገባት በመናገር ላይ ይገኛሉ።
አሜሪካ እንደ ከዚህ ቀደሙ እስራኤል ከአጸፋዊ ምላሽ እንድትቆጠብ እየመከረች ሳይሆን ይልቁንም ምላሹ ሊያስከትል የሚችለውን ውጥረት ለመቀነስ ሙከራዎችን እያደረገች ነው።
ሮይተርስ እንደዘገበው ቴልአቪቭ ታደርሰዋለች ተብሎ የሚጠበቀው ጥቃት ኢራን ባሳለፍነው አመት ሚያዚያ ወር ላይ ከፈጸመችው ጥቃት በአይነቱ እና በመጠኑ ሊጨምር ይችላል።
ቀዳሚ ኢላማ ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁት ደግሞ የኢራን የኒውክሌር ማብለያ እና የነዳጅ ማውጫ ጣብያዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ተጠቅሷል።
የመካከለኛው ምስራቅ በስለት ጫፍ ላይ እየተጓዘ ይገኛል ያሉት የአሜሪካ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ከርት ካምቤል ቀጠናዊ ግጭትን የሚያስከትሉ አካሄዶችን ለመከላከል ሁሉም አካላት ጥረት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
እስራኤል ከምድር ስር በሚገኙት የኒውክሌር ጣብያዎች ላይ ጥቃት ብትፈጽም በምድር ውስጥ ከሚገኙበት ርቀት አንጻር ሊደርስ የሚችለው ጉዳት ዝቅተኛ እንደሆነ የሚናገሩት ወታደራዊ ተንታኞች፤ የቴልአቪቭ ሚሳኤሎች ተሳክቶላቸው የኒውክሌር ጣብያዎችን ሰርስረው ከገቡ ግን የሚደርሰውን ጉዳት መገመት አስቸጋሪ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል።
ከአምስት በላይ የኒውክሌር ማብላያ ጣብያዎች እንዳሏት የሚነገርላት ኢራን በአሁኑ ወቅት በሁለት የኒውክሌር ጣብያዎቿ እያብላላችው የምትገኝው ዩራኒየም ለጦር መሳርያነት አገልግሎት ለመስጠት 60 በመቶ መጠጋቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ።