1,840 መኖሪያ ቤቶች እና 547 የንግድ ቤቶች ሙሉ ለሙሉ መውደማቸው ተገልጿል
በደቡብ ክልል ምዕራብ ኦሞ ዞን፣ ቤሮ ወረዳ፣ ሾላ ቀበሌ ትላንት በተከሰተ የእሳት አደጋ ከ586 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙ ተገለጸ።
የእሳት አደጋው ትላንት ታኅሣሥ 19 ቀን 2013 ከቀኑ11:00 ሰዓት አካባቢ ሾላ ቀበሌ ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።
በቀበሌው በተከሰተው የእሳት አደጋ 16 ሺህ 709 ነዋሪዎች እንደተፈናቀሉም አስተዳዳሪው ተናግረዋል።
በአካባቢው የባንክ አገልግሎት ባለመኖሩ ፣ ጥሬ ገንዘብን ጨምሮ በአደጋው 1ሺህ 840 መኖሪያ ቤቶች እና 547 የንግድ ቤቶች ሙሉ ለሙሉ መውደማቸውን የቤሮ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ዶንተስ ባይከን ተናግረዋል፡፡
መንስኤው እየተጣራ ሲሆን በወረዳው በወርቅ ስራ የሚተዳደሩ 37 ማኅበራት ንብረታቸው ሙሉ ለሙሉ መውደሙንም አመልክተዋል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።
ለተጎጂዎች የሰብአዊ እርዳታ እየተሰጠ መሆኑንና ተጨማሪ ድጋፎች ከፌዴራል እና ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልላዊ መንግሥት እንዲደረግላቸው የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ዶንተስ ጥሪ አቅርበዋል።