የተተኳሽ ሮኬት ማስወንጨፊያ ከባድ ተሽከርካሪም ከመቐለ ከተማ ዳርቻ ላይ ተደብቆ ተገኝቷል
የሕወሓት ቡድን በተደጋጋሚ ወደ ባሕር ዳር፣ ጎንደር እና አስመራ ሲያስወነጭፋቸው የነበሩት ተተኳሽ ሮኬቶች በመቐለ ከተማ በግለሰብ መጋዘን ውስጥ ተከማችተው መገኘታቸውን የልዩ ዘመቻ ኮማንድ አስታወቀ።
የመከላከያ ሠራዊት መቐለ ከተማን ከተቆጣጠረ በኋላ የልዩ ዘመቻ ኮማንድ 2ኛ ብርጌድ አንደኛ ወጋገን ሻለቃ ባደረገው አሰሳ እና ፍተሻ በመጋዘን ውስጥ ያልተተኮሱ 13 ሮኬቶች የተገኙ ሲሆን፣ 7 ሮኬቶች ደግሞ ከማስቀመጫው ሳጥን ወጥተው መተኮሳቸውን አስታውቋል።
በተጨማሪም የተተኳሽ ሮኬት ማስወንጨፊያ ከባድ ተሽከርካሪ ከመቐለ ከተማ ዳርቻ ባለ ስፍራ ተደብቆ ተገኝቷል።
የልዩ ዘመቻ ኮማንዶ 2ኛ ብርጌድ አንደኛ ወጋገን ሻለቃ ምክትል አዛዥ ሻምበል ኢያሱ ሽመልስ፣ ውጊያ አጠናቅቀው ወደ መቐሌ ከተማ ከገቡበት ቀን አንሥቶ ባደረጉት የቤት ለቤት አሰሳ መጋዘኑ መገኘቱን ተናግረዋል።
ሕወሓት የግለሰብ መጋዘን ሲጠቀም እንደነበር ጠቁመው፣ “በሲቪል ሕዝብ መጋዘን ውስጥ ሕዝብን ለመጨረስ አጥፊ መሣሪያ እያስቀመጡ ‘የሕዝብ ወገን ነኝ’ ማለት አይቻልም” ብለዋል።
አያይዘውም በሕዝብ ገንዘብ በውድ ዋጋ የተገዙ ንብረቶችን ዘርፈው ወደ ሕዝብ ሲተኩሱ እንደነበሩ ሻምበል ኢያሱ ገልጸዋል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።
ሕወሓት ከመከላከያ ሠራዊት ጋር ሲዋጋ በነበረበት ወቅት ወደ ባሕር ዳር ሁለት ጊዜ ፣ ወደ ጎንደር አንድ ጊዜ እንዲሁም ወደ አስመራ ሁለት ጊዜ ሮኬቶችን መተኮሱ ይታወሳል፡፡