የጋዛው ጦርነት የሚቆም ከሆነ ሄዝቦላ በእስራኤል ላይ ጥቃት መሰንዘሩን እንደሚያቆም አስታወቀ
የቡድኑ ምክትል መሪ ጦርነቱ በዚህ የሚቀጥል ከሆነ የእስራኤል ትልልቅ ከተሞች በሮኬት ኢላማዎቻችን ውስጥ ናቸው ብለዋል
በእስራኤል እና በሂዝቦላ መካከል ያለው ውጥረት ወደ ለየለት ጦርነት እንዳያመራ ከፍተኛ ስጋት አንዣቧል
የጋዛው ጦርነት የሚቆም ከሆነ ሄዝቦላ በእስራኤል ላይ ጥቃት መሰንዘሩን እንደሚያቆም አስታወቀ፡፡
የቡድኑ ምክትል መሪ ሼክ ናይም ካሲም “በግጭቱ የተሳተፍነው ለሀማስ እና ለፍልስጤማውያን ያለንን አጋርነት ለማሳየት ነው፤ እስራኤል ውግያውን የምታቆም ከሆነ ያለምንም ውይይት እኛም ጥቃት ማድረሳችን እናቆማለን” ብለዋል፡፡
ከአሶሼትድ ፕረስ ጋር ለ40 ደቂቃ ያክል ቃለ ምልልስ ያደረጉት የቡድኑ ምክትል መሪ እስራኤል በጋዛ የምታካሂደውን ፍትሀዊ ያልሆነ ጦርነት የምትቀጥል ከሆነ በሊባኖስ እና እስራኤል ድንበር ምን ሊፈጠር እንደሚችል መገመት አትችልም ሲሉ ዝተዋል፡፡
ባለፈው ወር የእስራኤል መከላከያ በሊባኖስ ሙሉ ጥቃት ለመሰንዘር የሚያስችል ስትራቴጅ አዘጋጅቶ ማጠናቀቁን ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡
ይህን አስመልክቶ ምላሽ የሰጡት የሄዝቦላ ምክትል መሪ ሼክ ካሲም እስራኤል በሄዝቦላ ላይ ሙሉ ጦርነት የማወጅ አቅም የላትም ብለዋል፡፡
የተገደበ ጦርነት አደርጋለሁ በሚል በሊባኖስ ድንበር ውስጥ ገብታ የምትነቀሳቀስ ከሆነ ደግሞ ጦርነቱን ወደግዛቷ እንደምወስደው ልታውቅ ይገባል ነው ያሉት፡፡
እስራኤል ሙሉ ጦርነት የምታወጅ ከሆነ በጦርነቱ እነማን ሊሳተፉ እንደሚችሉ መቆጣጠር አትችልም ሲሉ የግጭቱ መጠን ሊሰፋ እንደሚችልም አስጠንቅቀዋል፡፡
የሄዝቦላ አጋር ናቸው የሚባሉ በመካከለኛው ምስራቅ የሚንቀሳቀሰው አክሲስ የተሰኘው ታጣቂ ቡድን እንዲሁም በኢራቅ ፣ በሶርያ እና የመን ያሉ ተዋጊዎች ኢራንን ጨምሮ በዚህ ጦርነት ሊሳተፉ እንደሚችል ስጋት አለ፡፡
ቴልአቪቭ በጋዛ ጦርነት ካወጀች አንስቶ ላለፉት 9 ወራት ከእስራኤል ጋር በተካረረ ውጥረት ውስጥ የሚገኘው ሄዝቦላ ለሃማስ ያለውን ድጋፍ ለማሳየት በእስራኤል ላይ የተለያዩ የሮኬት እና የድሮን ጥቃቶችን ሰንዝሯል፡፡
ሁሉቱ አካላት የሚገኙበት ሁኔታ ወደ ለየለት ጦርነት ተቀይሮ ቀጠናዊ ግጭትን እንዳያስከትል አለም አቀፉ ማህበረሰብ ስጋቱን እየገለጸ ይገኛል፡፡
ሆኖም ሁሉቱም አካላት እርስ በእርስ የሚሰጧቸው መግለጫዎች እና ወታደራዊ ዝግጅቶች የጦርነቱን አይቀሬነት የሚያሳብቁ ናቸው ያሉ ተንታኞች ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ምን ሊፈጠር እንደሚችል በመተንተን ላይ ናቸው፡፡
በእስራኤል እና ሄዝቦላ መካከል ዝቅተኛ ነው በሚባለው አሁን ባለው ግጭት በሁለቱም ወገን ድንበር ላይ የሚኖሩ በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሀን ሲፈናቀሉ በሊባኖስ በኩል 450 ንጹሀን ሰዎች እና ታጣቂዎች ተገድለዋል በእስራኤል በኩል ደግሞ 16 ወታደሮች እና 11 ንጹሀን ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡
ሀማስ በጋዛ ያለው ጦርነት እንዲቆም እና ስምመነት ላይ እንዲደረስ ፍላጎት ያለው ሲሆን ለዚህም አለም አቀፉ ማህበረሰብ በእስራኤል ላይ ጫና እንዲያሳድር በመጠየቅ ላይ ይገኛል፡፡
ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔትንያሁ በበኩላቸው የሀማስ ወታደረዊ እና የአስተዳደር አቅም ሳይበታተን የጋዛው ጦርነት አይቆምም በሚለው አቋማቸው ጸንተዋል፡፡