እስራኤል በጋዛ የምድር ውጊያ ከጀመረች ከባድ ዋጋ ትከፍላለች - ሄዝቦላህ
የሊባኖሱ ሄዝቦላህ ምክትል መሪ ሼክ ናይም ካሴም ቡድኑ የእስራኤል ጦርን እያዳከመ መሆኑን ገልጸዋል
በእስራኤል ጦር የተገደሉ የሄዝቦላህ ታጣቂዎች ቁጥር 19 ደርሷል
እስራኤል በጋዛ የምድር ውጊያ ከጀመረች ከባድ ዋጋ እንደምትከፍል የሊባኖሱ ሄዝቦላህ ገልጿል።
የቡድኑ ምክትል መሪ ሼክ ናይም ካሴም ማስጠንቀቂያ የተሰማው የእስራኤል ጦር በደቡባዊ ሊባኖስ በፈጸመው ጥቃት ስድስት የሄዝቦላህ ተዋጊዎች በተገደሉበት በትናንትናው እለት ነው።
“የእስራኤልን ጦር ለማዳከም ጥረት እያደረግን ነው፤ ዝግጅታችን ምን እንደሚመስልም አሳይተናቸዋል” ብለዋል ምክትል መሪው።
ባለፈ ሳምንት ወደ ሊባኖስ ያቀኑ የፈረንሳይ እና ጀርመን ልኡካን ሄዝቦላህ በእስራኤልና ሃማስ ጦርነት እጁን እንዳያስገባ ቢጠይቁም ቡድኑ ለሊባኖስ መንግስት “እኛ የጦርነቱ አካል ነን” የሚል ምላሽ መስጠቱንም አብራርተዋል።
በኢራን የሚደገፈውና በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶች፣ ሚሳኤሎች እና የተለያዩ ድሮኖች የታጠቀው ሄዝቦላህ በሰሜናዊ እስራኤል አዲስ የጦር ግንባር እንደሚከፍት ይጠበቃል።
እስራኤልም በድንበር ላይ በርካታ ታንኮች እና ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን ተክላ እየተጠባበቀች ነው።
የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ ለፍልስጤሙ ቡድን አጋርነቱን ያሳየው ሄዝቦላህ በየቀኑ ወደ እስራኤል ሮኬቶችን ከመተኮስ አላረፈም።
ይህም እስራኤል ከሊባኖስ በሚያዋስናት ድንበር አቅራቢያ ባሉ ከተሞች የሚኖሩ ሰዎችን ቀያቸውን ለቀው እንዲወጡ እንድታሳስብ ምክንያት መሆኑን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
የሊባኖሱ ብሄራዊ የዜና ወኪል ናሽናል ኒውስ ኤጀንሲ በበኩሉ እስራኤል ሴጁድ በተባለችው ከተማ ላይ የድሮን ጥቃት መፈጸሟን አስታውቋል፤ ይህም የሊባኖስ እና እስራኤልን ውጥረት እንዳያንረው ስጋት ፈጥሯል።
ባለፉት ሁለት ሳምንታት የተገደሉ የሄዝቦላህ ታጣቂዎች ቁጥር 19 መድረሱ የተነገረ ሲሆን፥ ቡድኑ የተጠናከረ ውጊያ ለመጀመር እስራኤል በጋዛ የምትጀምረውን የምድር ውጊታ በመጠባበቅ ላይ ነው።
16ኛ ቀኑን በያዘው የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ከ4 ሺህ 300 በላይ ፍልስጤማውያን እና ከ1 ሺህ 400 በላይ እስራኤላውያን ህይወት አልፏል።