እስራኤል ሄዝቦላህ ጥቃቱን ካላቆመ የሊባኖስን ድንበር ጥሳ እንደምትገባ አስጠነቀቀች
ከሄዝቦላህ ጋር ለመነጋገር ረፍዷል ያለችው ቴል አቪቭ ከሊባኖሱ ቡድን ጋር ጦርነት ለመጀመር ተቃርባለች
እስራኤል በሊባኖስ በፈጸመቻቸው ጥቃቶች ከ100 በላይ ሰዎች ተገድለዋል
እስራኤል በሊባኖሱ ሄዝቦላህ ላይ የተጠናከረ እርምጃ እንደምትወስድ ገለጸች።
ቡድኑ በእስራኤል ላይ ጥቃት ማድረሱን ከቀጠለ የሊባኖስ ድንበርን ጥሰን ገብተን እርምጃ ለመውሰድ እንገደዳለን ነው ያሉት የእስራኤል የጦር ካቢኔ አባሉ ቤኒ ጋንዝ።
ጋንዝ “ከሄዝቦላህ ጋር ለመነጋገር ረፍዷል፤ በሰሜኑ ግንባር ያለው አካሄድ መቀየር አለበት” ማለታቸውም ቴል አቪቭ ከሊባኖሱ ቡድን ጋር የለየለት ጦርነት ውስጥ ለመግባት መዘጋጀቷን ያሳያል ተብሏል።
የእስራኤል ጦርም በሰሜኑ ግንባር ወታደሮች “በከፍተኛ ዝግጅት በተጠንቀቅ ላይ ናቸው” የሚል መግለጫን አውጥቷል።
ለፍልስጤሙ ሃማስ አጋርነቱን የገለጸው ሄዝቦላህ የጋዛው ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ በየእለቱ ወደ እስራኤል ሮኬቶችን በመተኮስ ላይ ነው።
በዚህም እስካሁን 13 እስራኤላውያን ህይወታቸው ማለፉ የተነገረ ሲሆን፥ እስራኤል በወሰደችው እርምጃም ከ100 በላይ ሊባኖሳውያን ህይወታቸው አልፏል።
በፈረንጆቹ 2006 ከእስራኤል ጋር ጦር የተማዘዘው ሄዝቦላህ በኢራን እንደሚደገፍ የሚነገር ሲሆን በሊባኖስ ፖለቲካ ውስጥ ተጽዕኖው የበረታ ነው።
የጥቅምት 7ቱን የሃማስ ጥቃት ያወደሰው ሄዝቦላህ ከሮኬት ጥቃቱ ባሻገር ድሮኖችን መጠቀም በመጀመሩም እስራኤል የድንበር ቁጥጥሯን አጠናክራለች።
የእስራኤል የጦር አውሮፕላኖች እና ሄሊኮፕተሮች በሊባኖስ ድንበር ደጋግመው መታየታቸውም የሚጀመርበት ቀን እንጂ ጦርነቱ አይቀሬ መሆኑን ያመላክታል ይላል የሬውተርስ ዘገባ።
ቡድኑን በፋይናንስና የጦር መሳሪያ የምታግዘው ቴህራንም በሶሪያ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኗን ገድላለች ባለቻት እስራኤል ላይ የበቀል እርምጃ እወስዳለሁ ማለቷ ይታወሳል።
የቴህራን የአጻፋ እርምጃ በቀጥታ አልያም እንደ ሄዝቦላህ እና ሃውቲ ባሉ ታጣቂ ቡድኖች ሊፈጸም እንደሚችልም ፍንጭ ሰጥታለች።
ከ21 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያንን ህይወት የቀጠፈው የጋዛው ውጥረት በቀጠለበት ሁኔታ እስራኤል ከሊባኖሱ ሄዝቦላህ ጋር አዲስ የጦርነት ግንባር መክፈቷ የጦርነቱን አድማስ ከማስፋት ባሻገር ከፍተኛ የሰብአዊ ቀውስ ማስከተሉ እንደማይቀር እየተነገረ ነው።