ቀጣዩ የሄዝቦላህ መሪ እንደሚሆን ሲጠበቅ በእስራኤል የተገደለው ሀሺም ሰይፈዲን ማን ነው?
ከሄዝቦላ ምክትል መሪ ቀጥሎ የቡድኑ ከፍተኛ ባለስልጣን እንደሆነ የሚነገርለት ሰይፈዲን ወታደራዊ ዘመቻዎችን በመምራት ዋና ሰው ነበር
ሰይፈዲን በሄዝቦላህ ውስጥ የነበረው ሀላፊነት ከአንድ ጠቅላይ ሚንስትር ጋር የሚስተካከል ነበርም ተብሏል
እስራኤል ከሀማስ እና ከሄዝቦላህ ጋር እያደረገች በምትገኘው ውግያ የቡድኖቹን ከፍተኛ መሪዎች መግደሏን ቀጥላለች፡፡
በትላንትናው ዕለት ደግሞ የእስራኤል ጦር ከሂዝቦላህ ጋር ባደረገው ውጊያ በሃሰን ናስራላህ ምትክ ሄዝቦላህን ይመራል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረውን ሀሺም ሰይፈዲን መግደሉን አረጋጧል።
ሰይፈዲን ከታዋቂ የሊባኖስ የሺዓ ቤተሰብ የተወለዱ ሲሆን የትውልድ ስፍራቸውም በሀገሪቱ በብዛት የሺዓ እምነት ተከታዮች በሚበዙበት የደቡብ ክፍል ነው።
በፈረንጆቹ በ1990ዎቹ ወደ ሊባኖስ ከመመለሳቸው በፊት በሄዝቦላህ ውስጥ የመሪነት ሃላፊነትን ለመውሰድ በኢራን ከተማ ቋም ውስጥ በሚገኙ ሃይማኖታዊ ትምህርት ቤቶች ተምረዋል።
የሄዝቦላህ ዋነኛ ደጋፊ ከሆነችው ኢራን ጋር ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን በተጨማሪም ልጃቸው የቀድሞ የኢራን አብዮታዊ ዘብ ጠባቂ መሪ ጄነራል ቃሲም ሱሊማን ሴት ልጅን አግብቶ ነበር፡፡
የናስራላህ ዘመድ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ሰይፈዲን በፈረንጆቹ 27 ናስራላህ በእስራኤል ከተገደለ ጀምሮ ቡድኑን ከምክትል መሪው ናይም ቃሴም ጋር በጋራ ሲመሩ ቆይተዋል።
ሃሺም ሰይፈዲን ወታደራዊ ዘመቻዎችን በመምራት እና በማስተባበር ሀላፊነት ባለው “የጂሃድ ካውንስል” ውስጥ በመሳተፍ ከፍተኛ ሚናን ሲጫወቱ ሰንብተዋል፡፡
በተጨማሪም በኢራን ለሚደገፈው ቡድን የፋይናንስ እና አስተዳደራዊ ጉዳዮችን የሚከታተል የስራ አስፈፃሚው ምክር ቤት ኃላፊ ነበሩ።
በዚህ ሃላፊነት ስፍራ ውስጥም ሰይፈዲን በጤና አጠባበቅ ፣ በትምህርት ፣በባህል እና በግንባታ እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ላይ የተሰማሩ የሄዝቦላህ ተቋማትን በሃላፊነት በመምራት ከመንግስት ጠቅላይ ሚንስትር ጋር የሚመሳሰል ሚና ይጫወቱ እንደነበር ይነገራል፡፡
የሀሺም ሰይፈዲን ሞት በሄዝቦላህ የሚረጋገጥ ከሆነ በእስራኤል በርካታ መሪዎቹ እና ወታደራዊ አዛዦቹ በተገደሉበት ቡድን ላይ ሌላ ትልቅ ጉዳት የሚያስከትል ነው ፡፡
በእስራኤል ጦር መሞታቸው የተረጋገጠው ሰይፈዲን በእስራኤል ዘንድ እንደ ናስራላህ ባይታወቁም ሀገሪቱ የአሸባሪ ድርጅት ብላ በምትጠራው ቡድን ግንባር ቀደም ኢላማ ውስጥ ይገኛሉ፡፡
ከዚህ ባለፈም ባለፈው አንድ አመት ሀሰን ናስረላህ በደህንነት ስጋት በማይገኝባቸው የከፍተኛ አመራሮች የቀብር ስነስርአት እና ሌሎች ሁነቶች ላይ በመታደም የቡድኑን አቋም ሲያንጸባርቁ በሰፊው ታይተዋል፡፡
ጥቅምት 7 ሀማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት ሲፈጽም በይፋ ወጥተው “የሄዝቦላህ ሮኬት እና ጠብመንጃዎች ከሀማስ ጎን ይሰለፋል” በሚል የቡድኑን ድጋፍ በግልጽ ያወጁትም ሰይፈዲን ነበሩ፡፡
የቀድሞ የሄዝቦላህ መሪ ሀሰን ናስረላህ ሀሺም ሰይፈድንን ከሌሎች ሀላፊዎች በተለየ በሚስጥራዊ ጉዳዮች ላይ ያማክሯቸው እንደነበር እንዲሁም ከበድ ከበድ ያሉ ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮዎችንም ይቀበሉ እንደነበር በቀጠናው ላይ የሚያጠኑ ተንታኞችን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል