እስራኤል የሟቹን የሄዝቦላ መሪ ነስረላህን ተተኪ መግደሏን አረጋገጠች
የእስራኤል ጦር እንደገለጸው ሰይፈዲን የተገደለው ከሶሰት ሳምንት በፊት በቤይሩት ከተማ ደቡባዊ ዳርቻ በተፈጸመ የአየር ጥቃት ነው
ሰይፈዲን ባለፈው አንድ አመት በተካሄዱ ግጭቶች ወቅት ነስረላህ በሌለበት ወቅት ንግግር በማድረግ ዋሳኝ ሚና ይዞ ነበር
እስራኤል የሟቹን የሄዝቦላ መሪ ነስረላህን ተተኪ መግደሏን አረጋገጠች።
እስራኤል ባለፈው ወር በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት በፈጸመችው የአየር ጥቃት የተገደለውን የሄዝቦላ መሪ ሀሰን ነስረላህን ይተካል የተባለውን ሀሽም ሰይፈዲንን መግደሏን ትናትንት አረጋግጣለች።
የእስራኤል ጦር እንደገለጸው ሰይፈዲን የተገደለው ከሶሰት ሳምንት በፊት በቤይሩት ከተማ ደቡባዊ ዳርቻ በተፈጸመ የአየር ጥቃት ነው።
በዚህ ወር መጀመሪያ እስራኤል ሰይፈዲን ሳይገደል አይቀርም የሚል መግለጫ አውጥታ ነበር። ሄዝቦላ እስራኤል ሰይፈዲንን ገድየዋለሁ በሚል ላወጣችው መግለጫ መልስ አልሰጠም።
"ነሰረላህን፣ ተተኪውን እና የሄዝቦላን ከፍተኛ አመራር አስወግደናል። ለእስራኤል ዜጎች ደህንነት ስጋት የሆነ ማንኛውም ሰው አያመልጠንም" ሲሉ የእስራኤል ጦር አዛዥ ሌፍትናንት ጀነራል ኸርዚ ሀለቬ ተናግረዋል።
እስራኤል በድንበር አካባቢ በመካከለኛው ምስራቅ የኢራን ጠንካራ አጋር ከሆነው ከሄዝቦላ ጋር ለአንድ አመት ያህል የተኩስ ልውውጥ ካደረገች በኋላ በሊባኖስ ላይ የእግረኛ እና የአየር ጥቃት ከፍታለች። ሄዝቦላ ወደ እስራኤል መተኮስ የጀመረው፣ በጋዛ ከእስራኤል ጋር እየተዋጋ ላለው ሀማስ አጋርነት ለማሳየት ሲሆን ሄዝቦላ አሁን ላይ ከፍተኛ አመራሮቹ በመገደላቸው ችግር ውስጥ ገብቷል።
የነስረላህ ዘመድ የሆነው ሰይፈዲን ወታደራዊ ዘመቻዎችን የሚቆጣጠረው የጂሀድ ካውንስል አባል እና የሄዝቦላን የፋይናንስ እና የአስተዳደር ጉዳዮች የሚቆጣጠረው የስራ አስፈጻሚ ካውንስል አባል ሆኖ ተሾሞ ነበር።
ሰይፈዲን ባለፈው አንድ አመት በተካሄዱ ግጭቶች ወቅት ነስረላህ በሌለበት ወቅት በቀብር ስነ ሰርአቶች እና በሌሎች ሁነቶች ላይ እየተገኘ ንግግር በማድረግ ዋሳኝ ሚና ይዞ ነበር።
እስራኤል በርካታ የሀማስ መሪዎችን እና መሰከረም 27 በፈጸመችው የአየር ጥቃት ተጽዕኖ ፈጣሪውን የሄዝቦላ መሪ ነስረላህን ከገደለች በኋላም ቢሆን በጋዛ እና በሊባኖስ የምታደርገውን ዘመቻ የመቀነስ ፍላጎት አላሳየችም።
ዲፕሎማቶች እስራኤል ከህዳሩ የአሜሪካ ምርጫ በፊት ወሳኝ ቦታዎች የመያዝ አላማ እንዳላት ተናግረዋል።
የእስራኤል-ሄዝቦላ ጦርነት ኢራን እና የእስራኤል አጋር የሆነችውን አሜሪካን ወደ ጦርነቱ ጎትቶ ያስገባል የሚል ስጋት ፈጥሯል።
ኢራን በእስራኤል ላይ የሚሳይል ናዳ ያዘነበችው የእስራኤልን የሊባኖስ ወረራ እና የሄዝቦላ መሪ ሀሰን ነስረላህግ ግድያ ለመበቀል ነበር።
ጥቃቱን ተከትሎ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ "ኢራን ከባድ ስህተት ሰርታለች፤ ዋጋ ትከፍላለች" እና የእስራኤል ረጅም እጅ ኢራን ውስጥ የማይደርስበት ቦታ የለም" የሚሉ ዛቻዎችን ማሰማታቸው ይታወሳል።
ቀኑ አይታወቅ እንጂ እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት ለመክፈት ዝግጅቷን ጨርሳለች።
ኢራን በበኩሏ እስራኤል ጥቃት የምትሰነዝርባት ከሆነ የአጸፋ ምላሿ የከፋ እንደሚሆን ዝታለች።