በሊባኖስ የሬድዮ መገናኛዎች ላይ በተመሳሳይ ሰዓት በደረሰ ሁለተኛ ዙር ፍንዳታ 20 ሰዎች ሞቱ
የሬድዮ መገናኛዎች ፈንዳታው ከሞቱት ሰዎች በተጨማሪ ከ450 በላይ ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል
በእጅ የሚያዙት የሂዝቦላህ ታጣቂዎች የሬዲዮ መገናኛዎቹ ቤሩትን ጨምሮ በመላው ሊባኖስ በተመሳሳይ ሰዓት ነው የፈነዱት
በሊባኖስ በሄዝቦላህ ታጣቂዎች የሬድዮ መገናኛዎች ላይ በተከሰተ ሁለተኛ ዙር ፈንዳታ 20 ሰዎችን መግደላቸው ተነገረ።
የሬዲዮ መገናኛ ፍንዳታው የተከሰተው በትናትናው እለት “ፔጀር” በመባል የሚታወቁት የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ ላይ ካጋጠመ ፍንዳታ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።
የሬዲዮ መገናኛ ፍንዳታው ካጋጠመባቸው ስፍራዎች መካከል አንዱ በትናነትናው እለት በ“ፔጀር” ፍንዳታ ህይወቱ ያለፈ የሄዝቦላህ አባል የቀብር ስነ ስርዓት ላይ ነው።
በስፍራው ላይም ህጻናትና አዛውንቶችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱ ነው የአይን እማኞች የተናገሩት።
የሊባኖስ የጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ከሆነ ትናንት በደረሰው ፍንዳታ የ20 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ፤ 450 ሰዎች ላይ ደግሞ የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት ደርሷል።
ጤና ሚኒስቴሩ አክሎም ማክሰኞ እለት “ፔጀር” በመባል የሚታወቁት የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ ፍንዳታ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 12 መድረሱን እና ሁለት ህጻናትን ጨምሮ 3000 ገደማ ሰዎች መቁሰላቸውን አስታውቋል።
የእስራኤል ባለስልጣናት በሬዲዮ መገናኛዎቹ ፍንዳታ ላይ እስካሁን አስተያየት ያልስጡ ሲሆን፤ ምንጮች ግን ለዚህ አይነቱ ውስብስብ ጥቃት የእስራኤሉ የስለላ ተቋም “ሞሳድ” ተጠያቂ ነው እያሉ ነው።
አንድ የሄዝቦላህ ኃላፊ በጉዳዩ ላይ በሰጡት አስተያየት፤ ጥቃቱ በቡድኑ ታሪክ ውስጥ ትልቁ የደህንነት አደጋ ነው ሲሉ ገልጸውታል።
የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት በፍንዳታው ዙሪያ አስተያየት ባይሰጡም፤ “በሰሜን በኩል አዲስ የጦርነት ምእራፍ እየከፈትን ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
“በፍንዳታው ውስጥ እጄ የለበትም” ያለችው አሜሪካ፤ ግጭቶችን ለማስቀረት ከፍተኛ የሆነ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እያደረገች መሆኑን አስታውቃለች።
በትናንትናው እለት በተመሳሳይ ሰዓት የፈነዱት የሬዲዮ መገናኛዎች ከ5 ወራ በፊት በሄዝቦላህ የተገዙ መሆናቸውን የደህንነተ ምንጮች ለሮይተረስ ተናግረዋል።
ማክሰኞ እለት “ፔጀር” በመባል የሚታወቁት በእጅ የሚያዙ የኤሌክትሮኒክስ የመገናኛ መሳርያዎች በተመሳሳይ ሰዓት ፈንድተው ጉዳት ማስከተላቸው ይታወሳል።
ሄዝቦላ መገናኛ ዘዴዎች በምን አይነት ሁኔታ ወደ ፈንጂነት እንደተቀየሩ ምርመራዎችን እያደረገ እንደሚገኝ ገልጾ ከጥቃቱ ጀርባ ግን የእስራኤል እጅ እንደሳለበት ወንጅሏል፡፡
የመገናኛ መሳሪያዎቹ በተጠቃሚዎቹ ኪስ ውስጥ እና በእጅ ላይ እንዳሉ መፈንዳታቸው ሲገለጽ የፈነዱበት ሰአት ተመሳሳይ መሆን ድንገተኛ ሳይሆን በተቀነባበረ መንገድ የተፈጸመ ጥቃት መሆኑን አመላካች ነው ተብሏል።
“ፔጀርስ” በመባል የሚታወቁት የመገናኛ ዘዴዎች ምርታቸው ቆየት ያለ የመገናኛ ዘዴዎች ሲሆኑ እስራኤል የሞባይል ስልኮችን በመጥለፍ የሄዝቦላ አባላትን በተደጋጋሚ ኢላማ በማድረግ ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ ነው በቡድኑ ዘንድ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ የሚገኙት።