ሂዝቦላ በዛሬው እለት ወደ ሰሜናዊ እስራኤል ሮኬት በመተኮስ የአጸፋ ምላሽ ሰጥቷል
እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ በፈጸመችው የአየር ጥቃት የሂዝቦላ የልዩ ሀይል መሪን ገደልኩ አለች፡፡
የእስራኤል መከላከያ ሀይል ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት ሞሀመድ ቃሲም የተባለው የልዩ ሀይል አዛዥ በእስራኤል የሚፈጸሙ የሽብር ጥቃቶችን በማስተባበር ዋነኛ ከነበሩ ወታደራዊ መሪዎች መካከል አንዱ ነው ተብሏል፡፡
በተጨማሪም ትላንት ምሽት ላይ በተፈጸመ ጥቃት ለእስራል ስጋት ናቸው የተባሉ 30 ማዘዣ ጣብያዎች እና ወታደራዊ መሰረተ ልማቶችን ማውደሙን ገልጿል፡፡
የወታደራዊ መሪው መገደሉን ያረጋገጠው ሂዝቦላ በሰሜናዊ እስራኤል ሁለት ቦታዎች ላይ የሮኬት ጥቃት በመፈጸም የአጸፋ ምላሽ መስጠቱን አስታውቋል፡፡
የሊባኖስ መገናኛ ብዙሀን እንደዘገቡት ምሽቱን አልካሊህ በተባለ ከተማ የደረሰው ጥቃት በመሰረተ ልማቶች ፣ ህንጻዎች እና ሰብሎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፡፡
በአየር ጥቃቱ እስካሁን የሞቱ ሰዎች ስለመኖራቸው በግልጽ የተባለ ነገር ባይኖርም 12 ሰዎች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው በህክምና ተቋማት እንደሚገኙ ተሰምቷል፡፡
የአሁኑ የአየር ጥቃት ከሳምንታት በፊት እስራኤል በድሮን ጥቃት የሂዝቦላን ከፍተኛ ወታደራዊ መሪ ፉአድ ሹክርን ከገደለች በኋላ የተደረገ ነው፡፡
ይህንንም ተከትሎ ይህ አመት እስራኤል ከ2016 ወዲህ ለመጀመርያ ጊዜ ሁለት የሂዝቦላ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮችን የገደለችበት ሆኗል፡፡
የጋዛ ጦርነት መጀመሩን ተከትሎ እስራኤል እና ሂዝቦላ መጠነ ሰፊ የተኩስ ልውውጥ እያደረጉ የቀጠሉ ሲሆን የሀማስ የፖለቲካ መሪ እስማኤል ሀኒየህ ከተገደሉ በኋላ ደግሞ ቀጠናዊ ውጥረቱ ወደለየለት ጦርነት እንዳያመራ ከፍተኛ ስጋት አንዣቧል፡፡
በተመሳሳይ በትላንትናው ምሽት እስራኤል በዌስት ባንክ በፈጸመችው ጥቃት አምስት ሰዎች ተገድለዋል፡፡
በስፍራው የሀማስ ቡድን አባላት መሸሸጊያ ናቸው በተባሉ ቦታዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን የሀገሪቱ መከላከያ ሀይል አረጋግጧል፡፡
የአካባቢው ባለስልጣናት በአየር ጥቃቱ የተገደሉት በመስጂድ ውስጥ የነበሩ ከ15 -20 አመት የሚገኙ ያልታጠቁ ከሀማስ ጋር ግንኙነት የሌላቸው ወጣቶች ናቸው ብለዋል፡፡
ባለስልጣናቱ የእስራኤል ጦር በዌስት ባንክ በተደጋጋሚ ቤት ለቤት የሚያደርገው አሰሳ እና የሚፈጽማቸው የአየር ጥቃቶች በአካባቢው ከፍተኛ ስጋት እና ፍራቻን አንግሷል ነው ያሉት፡፡