ቤኒ ጋንዝ የእስራኤል ጦር ትኩረቱን ከጋዛ ወደ ሊባኖስ እንዲያዞር አሳሰቡ
የቀድሞው የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር “የሃማስ ጉዳይ ያለቀለት ነው፤ አሁን ትኩረታችን በሙሉ ወደ ሰሜን ሊሆን ይገባል” ብለዋል
እስራኤልና የሊባኖሱ ሄዝቦላህ ባለፉት 11 ወራት በየቀኑ ተኩስ ሲለዋወጡ ቢቆዩም እስካሁን ወደለየለት ጦርነት አልገቡም
እስራኤል ወታደራዊ ትኩረቷን ከጋዛ ወደ ሊባኖስ ልታዞር እንደሚገባ የእስራኤል የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትር ቤኒ ጋንዝ አሳሰቡ።
ጋንዝ በዋሽንግተን በተካሄደ የመካከለኛው ምስራቅ ፎረም ላይ ባደረጉት ንግግር፥ በጋዛ በቂ ሃይል ስለሚገኝ አሁን ላይ ትልቅ ትኩረት የሚሻው የሊባኖስ ድንበር ሁኔታ ነው ብለዋል።
ሃማስን “ያረጀ ዜና” ነው ሲሉ የገለጹት የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትር፥ ኢራን እና የምታስታጥቃቸው ሃይሎች ዋነኛ ስጋታችን ናቸው ብለዋል።
እስራኤል በአሁኑ ወቅት በጋዛ ያሻትን ማድረግ የሚያስችል አቅም መፍጠሯን በመጥቀስም ፈጣን እርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ አቅርበዋል።
በጋዛ ታግተው የሚገኙ እስራኤላውያንንም በስምምነት ለማስወጣት ቀናት ወይም ሳምንታትን ቢወስድ ነው ያሉት ቤኒ ጋንዝ፥ “አሁን ጊዜው ወደ ሰሜን የምንዘምትበት ነው፤ እንደኔ የዘገየን ይመስለኛል” ማለታቸውንም ታይምስ ኦፍ እስራኤል አስነብቧል።
የናሽናል ዩኒቲ ፓርቲ መሪው በሰኔ ወር ከጦር ካቢኔ ሚኒስትርነታቸው ከመልቀቃቸው በፊትና በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በድህረ ጋዛ ጦርነት ዙሪያ ግልጽ እቅድ የላቸውም በሚል ሲቃወሙ መቆየታቸው ይታወሳል።
ባለፈው ሳምንትም ከሊባኖስ ጋር በሚዋሰኑ የድንበር ከተሞች የተፈናቀሉ ከ60 ሺህ በላይ ሰዎችን በማስመለሱ ሂደት “ኔታንያሁ በግልጽ ዋሽቶናል” ማለታቸውን ዘ ናሽናል ኒውስ ዘግቧል።
በዋሽንግተኑ ንግግራቸው ግን በኔታንያሁ ላይ ትችት ከማብዛት ተቆጥበው ትኩረታችን ሁሉ ወደ ሊባኖስ ይሁን ሲሉ ተደምጠዋል።
እስራኤል በሊባኖስ ከህዳር 8 ጀምሮ በፈጸመችው የአየር ጥቃት 614 ሰዎች መገደላቸውን የአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ቆጠራ ያመላክታል። ከሟቾቹ ውስጥ አብዛኞቹ የሄዝቦላህ ተዋጊዎች መሆናቸው የተነገረ ሲሆን፥ 138 ንጹሃን ህይወታቸው ማለፉንም ዘገባው ጠቁሟል።
በእስራኤል በኩልም እስካሁን 24 ወታደሮች እና 26 ንጹሃን መገደላቸው ተገልጿል።
እስራኤላውያን ባለፈው ቅዳሜ 11ኛ ወሩን የደፈነው የጋዛው ጦርነት ቆሞ ታጋቾች እንዲለቀቁ በተቃውሞ ሰልፎች መጠየቃቸውን ቀጥለዋል።
ባለፈው ቅዳሜም በእስራኤል ታሪክ ከፍተኛ ነው የተባለ 750 ሺህ ሰዎች ለተቃውሞ አደባባይ የወጡበት ሰልፍ መካሄዱ የሚታወስ ነው።