“ፔጀር” በመባል የሚታወቁት በብዛት በሂዝቦላ ታጣቂዎች ጥቅም ላይ የሚውሉት የግንኙነት መሳርያዎች በተመሳሳይ ሰአት ፈንድተው ነው ጉዳት ያደረሱት
በሊባኖስ የሬድዮ መገናኛዎች ፈንድተው 9 ሰዎችን መግደላቸው ተነገረ።
“ፔጀር” በመባል የሚታወቁት በእጅ የሚያዙ የሬድዮ የመገናኛ መሳርያዎች በብዛት በሄዝቦላ ታጣቂዎች ዘንድ ጥቅም ላይ የሚውሉ ሲሆን በትላንትናው እለት በተለያዩ ስፍራዎች በተመሳሳይ ሰአት በመፈንዳት በሰዎች ላይ ጉዳት አድርሰዋል፡፡
ሄዝቦላ መገናኛ ዘዴዎች በምን አይነት ሁኔታ ወደ ፈንጂነት እንደተቀየሩ ምርመራዎችን እያደረገ እንደሚገኝ ገልጾ ከጥቃቱ ጀርባ ግን የእስራኤል እጅ እንደሳለበት ወንጅሏል፡፡
የመገናኛ ሬድኖዎቹ በተጠቃሚዎቹ ኪስ ውስጥ እና በእጅ ላይ እንዳሉ መፈንዳታቸው ሲገለጽ የፈነዱበት ሰአት ተመሳሳይ መሆን ድንገተኛ ሳይሆን በተቀነባበረ መንገድ የተፈጸመ ጥቃት መሆኑን አመላካች ነው ተብሏል፡፡
በዋና ከተማዋ ቤሩት ፍንዳታው በተፈጠረበት አካባቢ የሚገኙ በኢራን የሊባኖስ አምባሳደርን ጨምሮ 2800 ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱ ተሰምቷል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ ጉዳት የደረሰባቸው 200 ሰዎች በአስጊ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ የሀገሪቱ ጤና ሚንስቴር አስታውቋል፡፡
ብዙዎቹ ተጎጂዎችም ከወገብ በላይ በፊታቸው ፣ በአይን እና ደረታቸው አካባቢ ጉዳት ደርሶባቸዋል ነው የተባለው፡፡
በኢራን እንደሚደገፍ የሚነገረው ሂዝቦላ ከሟቾቹ መካከል ስምንቱ የቡድኑ ታጣቂዎች እና በተለያዩ ሀላፊነት ላይ የሚያገለግሉ አባላት እንደነበሩ አረጋግጧል፡፡
ይህን ጥቃት ከእስራኤል ውጭ ማንም ሊያቀነባብረው እንደማይችል በእርግጠኛነት የተናገረው ቡድኑ በቅርቡ ተመጣጣኝ ምላሽ እንደሚሰጥ መዛቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የእስራኤል መከላከያ ሚንስትር በጥቃቱ ዙሪያ እጁ እንዳለበት ለተጠየቀው ጥያቄ ምላሽ ከመሰጠት ተቆጥቧል፡፡
“ፔጀርስ” በመባል የሚታወቁት የመገናኛ ዘዴዎች ምርታቸው ቆየት ያለ የመገናኛ ዘዴዎች ሲሆኑ እስራኤል የሞባይል ስልኮችን በመጥለፍ የሄዝቦላ አባላትን በተደጋጋሚ ኢላማ በማድረግ ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ ነው በቡድኑ ዘንድ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ የሚገኙት፡፡
ፍንዳታው ከመፈጠሩ ከሰአታት በፊት የእስራኤል የደህንነት ካቢኔ በሰሜን ድንበር የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ መኖርያቸው ለመመለስ የሄዝቦላህን ጥቃት በቋሚነት ማስቆም ይጠበቅብናል የሚል መግለጫ አውጥተ ነበር፡፡
የጋዛውን ጦርነት መከሰት ተከትሎ እስራኤል እና ሂዝቦላ በየቀኑ በሚባል ደረጃ የሚሳኤል እና ሮኬቶች ተኩስ ልውውጥ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡