እስራኤል ሁለተኛውን የሂዝቦላህ ወታደራዊ አዛዥ ገደለች
አህመድ ዋህቢ የተሰኘው የሂዝቦላህ ኮማንድር በቤሩት በተፈጸመ የእስራኤል ጥቃት ተገድሏል ተብሏል
ኢብራሂም አኪል የተሰኘው ሌላኛው የሂዝቦላህ ወታደራዊ አዛዥ ትናንት መገደሉ ይታወሳል
እስራኤል ሁለተኛውን የሂዝቦላህ ወታደራዊ አዛዥ ገደለች፡፡
ከአንድ ዓመት በፊት የሐማስ ታጣቂዎች በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት መሰንዘራቸውን ተከትሎ የተጀመረው ጦርነት መልኩን ቀይሮ አሁን ላይ ወደ ሊባኖስ ፊቱን አዙሯል፡፡
የእስራኤል ጦር ከትናንት በስቲያ ጀምሮ በደቡባዊ ሊባኖስ በኩል ከፍተኛ የተባለ የአየር ላይ ጥቃት በማድረስ ላይ ትገኛለች፡፡
በትናንትናው ዕለት በሀገሪቱ መዲና ቤሩት ከተማ ባደረሰችው የአየር ላይ ጥቃት ኢብራሂም አኪል የተባለው የሂዝቦላህ ሬድዋን ሀይል ኮማንደር መግደሏ ይታወሳል፡፡
እስራኤል ከኢብራሂም በተጨማሪም አህመድ ዋህቢ የተባለውን የቡድኑን ከፍተኛ ወታደራዊ አመራር እንደገደለች ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
በመኖሪያ ቤት ላይ በተሰነዘረው በዚህ ጥቃት ከሁለቱ ወታደራዊ አዛዦች በተጨማሪ ከ60 በላይ ነዋሪዎች እንደቆሰሉም ተጠቅሷል፡፡
ሂዝቦላህ በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ በቤሩት በተፈጸመው የእስራኤል ጥቃት ምክንያት ከሁለቱ አመራሮች በተጨማሪ 15 ተዋጊዎቹ እንደተገደሉበት አስታውቋል፡፡
ግድያውን ፈጽመዋለች የተባለችው እስራኤል እስካሁን በይፋ ያለችው ነገር የሌለ ሲሆን በጋዛ የነበረው ውጊያ ወደ ሊባኖስ ማዞሯን አስታውቃለች፡፡
እስራኤል የሂዝቦላህ ከፍተኛ አመራር መካከል ባሳለፍነው ሀምሌ ወር ላይ ፉአድ ሽኩርን በደቡባዊ ሊባኖስ መግደሏ ይታወሳል፡፡
ኢብራሂም አኪል በፈረንጆቹ 1983 ላይ በቤሩት በሚገኘው የአሜሪካ ኢምባሲ በደረሰው የቦምብ ጥቃት እንዲሁም በዚሁ ተመሳሳይ ዓመት በሊባኖስ የነበሩ የአሜሪካ ባህር አባላት ላይ የተፈጸመውን ጥቃት አቀነባብሯል ተብሎ ይፈለግ ነበር፡፡
ይህን ተከትሎም አሜሪካ ኢብራሂም አኪልን ለጠቆመኝ 7 ሚሊዮን ዶላር እከፍላለሁ ስትል ማስታወቂያ አስነግራ ነበር፡፡