በእስራኤል እና በሄዝቦላህ መካከል ምን እየተካሄደ ነው? እስካሁን የምናውቀው
ሄዝቦላህ እና እስራኤል ዛሬ ከጠዋት ጀምሮ እስር በእርስ ጥቃት ተሰናዝረዋል
እስራኤል “የሄዝቦላህን የሮኬት ማስወንጨፊያ መታሁ” ስትል፤ ሄዝቦላህ “የእስራኤል የጦር ሰፈሮችን አጥቅቻለሁ” አለ
በሊባኖስ የሚንቀሳቀሰው ሄዝቦላህ የወታራዊ አዛዡን ግድያ ለመበቀል እስራኤል ላይ ጥቃት እንደሚሰነዘር ቢጠበቀም፤ እስራኤል ዛሬ ንጋት ላይ ጥቃቱን አስቀድማ ጀምራለች።
እስራኤል እና ሄዝቦላህ ዛሬ ከጠዋት ጀምረው በሊባኖስ እና እስራኤል ድንበር ላይ እርስ በእርሳቸው ጥቃት መሰናዘራቸውን ተከትሎ በመካለኛው ምስራቅ ያለው ስደጋት ተባብሷል።
ዛሬ የተፈጠረው ምንድን ነው?
የእስራኤል የጦር ጄቶች ዛሬ ማለዳ ላይ በደቡባዊ ሊባኖስ ላይ ጥቃት መሰንዘር የጀመሩ ሲሆን፤ እስራኤል ጥቃቱን ቀድማ የጀመረችውም እስራኤልን ለመምታት በዝግጅት ላይ በነበሩ የሂዝቦላህ ሮኬት ማስወንጨፊያዎችን ቀድሞ ለማውደም ነው ብላለች።
የእስራኤል ጦር ሄዝቦላህ ንጋት 11 ሰዓት ወደ መካከለኛው እስራኤል በመቶዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶችን ለመተኮስ በዝግጅት ላይ እንደሆነ እንደደረሰበት እና ጥቃቱ ከመሰንዘሩ 30 ደቂቃ ቀደም ብለው 100 የእስራኤል የጦር ጄቶች የሄዝቦላህ የሮኬት ማስወንጨፊያዎችን መምታታቸውን አስታውቋል።
ሄዝባላ በበኩሉ ባለፈው ወር በቤሩት በከፍተኛ ወታደራዊ አዛዡ ላይ የተፈጸመውን ግድያ ለመበቀል በዛሬው እለት በእስራኤል ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶች እና ድሮኖችን መተኮሱን አስታውቋል።
በጥቃቱ ማን ምንን መታ?
የሊባኖሱ ሄዝቦላህ 11 የእስራኤል ጦር መገልገያዎችን መምታቱን ያስታወቀ ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ ሜሮን የጦር ሰፈር እንደሚገኝበት አስታውቋል። በተጨማሪም በጎላን ተራራ ላይ የሚገኙ አራት ስፍራዎችን መምታቱንም አስታውቋል።
የእስራኤል ጦር በበኩሉ በሺዎች የሚቆጠሩ የሄዝቦላህ የሮኬት ማስወንጨፊያዎችን መምታቱን አስታውቋል።
አሁን ምን እየተካሄደ ነው?
በአሁኑ ሰዓት በአካባቢው ያለው ሁኔታ የተረጋጋ ይመስላል።
ሄዝቦላህ “እስራኤል የሮኬት ማስወንጨፊያዎቼን አልመታችም” ሲል ያስተባበለ ሲሆን፤ “የመጀሪያው ዙር የበቀል እስርምጃዬ ስኬታማ ነበር” ብሏል።
እስራኤል በሰሜናዊ የሀገሪቱ ክፍል ላይ የደህንነት መመሪያዎችን አውጥታለች፣ ነገሮች የተረጋጉ መምሰሉን ተከትሎም ለጥቂት ሰዓታት ተዘግቶ የነበረውን የቤን ጉሪዮን አውሮፕላን ማረፊያ እንደገና እየከፈተች ትገኛለች።
የሄዝቦላ ወታደራዊ አዛዥ ሹክር እና የሀማስ ፖለቲካዊ መሪ ሀኒየህን ግድያ ተከትሎ በመካከለኛው ምስራቅ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ውጥረት ተፈጥሯል።