ብሪታንያ የተወሰኑ የጦር መሳርያ አይነቶች ለእስራኤል እንዳይሸጡ ከለከለች
ሀገሪቱ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው የጦር መሳርያዎቹ የአለም አቀፍ ህግን ለመጣስ ሳይውሉ አይቀርም በሚል ነው
ውሳኔውን “አሳፋሪ” ሲሉ የገለጹት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ድርጊቱ ሀማስን እንደማበረታት የሚቆጠር ነው ብለዋል
ብሪታንያ ለእስራኤል ስትሸጣቸው ከነበሩ የጦር መሳርያዎች መካከል የተወሰኑት ከሽያጭ ዝርዝር ውስጥ እንዲወጡ ውሳኔ አሳልፋለች፡፡
ሀገሪቱ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው ለእስራኤል የምታቀርባቸው የጦር መሳርያዎች የአለም አቀፍ ህግን ለመጣስ ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ በሚል ነው፡፡
350 ከሚደርሱ የጦር መሳርያ ዝርዝሮች ውስጥ ፈቃዳቸው እንዲሰረዝ ወይም እንዳይሸጡ የታገዱት የጦር መሳርያዎች ቁጥር 30 እንደሚደርስ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የብሪታንያ የመከላከያ ሚኒስትር ጆን ሄሊ እንደተናገሩት የድሮን ፣ የውግያ ሄሊኮፕተሮች እና ጄቶች አካላት በክልከላው ውስጥ ተካተዋል፡፡
የእስራኤል 6 ታጋቾች በተገደሉበት በዚህ ወቅት ውሳኔው የተላለፈበት ጊዜ ምን ያህል ተገቢ ነው ተብለው የተጠየቁት የመከላከያ ሚኒስትሩ፥ ውሳኔው በህጋዊ ሂደቶች ውስጥ እያለፈ በመቆየቱ እንጂ ከተወሰነ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡
አስራኤል የጦር መሳርያዎች ከምታስገባባቸው ሀገራት መካከል ከብሪታንያ የምታስገባው አንድ በመቶ ብቻ ቢሆንም በጋዛ ለምትፈጽማቸው የአየር ላይ ጥቃቶች ክልከላ የተላለፈባቸው የጦር መሳርያዎች ወሳኝ ስለመሆናቸው ተነግሯል፡፡
ከ2019-2023 69 በመቶ የጦር መሳርያ ግዢን የፈጸመችባት አሜሪካ ትልቋ የእስራኤል ጦር መሳርያ አቅራቢ ናት፡፡ ብሪታንያ ከቴልአቪቭ በተጨማሪ ለቱርክ ፣ ሳኡዲ አረብያ እና ዩክሬን ጦር መሳርያዎችን ትሸጣለች፡፡
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዴቪድ ላሚ የጦር መሳርያዎቹ አለምአቀፋዊ የሰብአዊ መብት ህጎችን በማይጻረር መልኩ ጥቅም ላይ መዋላቸውን እስከምናረጋግጥ ድረስ ክለከላው ይጸናል ብለዋል፡፡
አምነስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ ብሪታንያ ለእስራኤል ከምታቀርበው የጦር መሳርያ ከ10 በመቶ ሽያጭ ያነሰ ክልከላ ማድረጓ “አስመሳይ የፖለቲካ ውሳኔ” ነው ብሎታል፡፡
አክሎም እገዳው የእስራኤል ጦር በጋዛ እያደረሰው በሚገኘው የሰብአዊ መብት ጥሰት እና የንጹሀን ግድያ ላይ ይህ ነው የሚባል ተጽእኖ እንደማይኖረው ገልጿል፡፡
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው ይህ ያልተጠና ውሳኔ ሃማስን ከማበረታት የዘለለ ሚና የሌለው “አሳፋሪ” ተግባር ነው ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም እስራኤል እገዳው ቢጣልባትም ሀማስን ማሸነፏ እና ጥቅሟን ማስከበሯ አይቀርም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡