የሄዝቦላህ ከፍተኛ አዛዥ ታሌብ አብደላህ በእስራኤል የአየር ጥቃት ተገደለ
በጥቃቱ ከታሌብ አብደላህ ጋር ለስብሰባ የተቀመጡ ሶስት የቡድኑ ተዋጊዎችም ህይወታቸው ማለፉ ተገልጿል
እስራኤል ባለፉት ስምንት ወራት ከ320 በላይ የሄዝቦላህ ተዋጊዎች መደምሰሷን ይፋ አድርጋለች
እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ በፈጸመችው የአየር ጥቃት የሄዝቦላህ ከፍተኛ አዛዥን መግደሏ ተነገረ።
ሂዝቦላህ ታሌብ አብደላህ ወይም አቡ ታሌብ የተባለው የቡድኑ ከፍተኛ አዛዥ መገደሉን አረጋግጧል።
ከታሌብ ጋር ጁያ በተባለች መንደር ስብሰባ ላይ የነበሩ ሶስት የቡድኑ ተዋጊዎችም በአየር ጥቃቱ መገደላቸውን ሬውተርስ የደህንነት ምንጮችን ጠቅሶ አስነብቧል።
ታሌብ አብደላህ ስምንተኛ ወሩን በያዘው የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ከተገደሉ የሄዝቦላህ አመራሮች ሁሉ በከፍተኛ ስልጣን ላይ የነበረ ነው ተብሏል።
በእስራኤል ድንበር አካባቢ የሚከናወኑ ዘመቻዎችን የሚመራው አቡ ታሌብ በጥር ወር በእስራኤል ከተገደለው ዋሲም ታዊል ከፍ ያለ ስልጣን የነበረው መሆኑንም ዘገባው አክሏል።
የእስራኤል ጦር አራት የሄዝቦላህ ተዋጊዎች ስለተገደሉበት ጥቃት እስካሁን ማብራሪያ አልሰጠም።
የሊባኖሱ ሄዝቦላህ የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ ወደ እስራኤል ሚሳኤሎችን በመተኮስ ለፍልስጤማውያን አጋርነቱን አሳይቷል።
በጥቃቱም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን ከድንበር ከተሞች ለቀው ለመውጣት መገደዳቸውን እስራኤል ትገልጻለች።
የሄዝቦላህ ጥቃት እያየለ መምጣትን ተከትሎም የእስራኤል ጄቶች ወደ ሊባኖስ እየዘለቁ በቡድኑ ይዞታዎች ላይ ድብደባ ሲፈጽሙ መቆየታቸው ይታወቃል።
ባለፉት ስምንት ወራትም ከ320 በላይ የቡድኑ ተዋጊዎች መገደላቸውን የእስራኤል ጦር አስታውቋል።
እስራኤል ባለፈው ጥር ወር በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤሩት በፈጸመችው የአየር ጥቃት የሀማስ ምክትል የፖለቲካ መሪ ሳሌህ አል አሩሪን መግደሏ ይታወሳል።
ቴል አቪቭ በንጹሃን ሊባኖሳውያን ላይ ያደረሰችውን ጉዳት ባትገልጽም የመንግስታቱ ድርጅት ከ80 በላይ ንጹሃን ህይወት መቀጠፉን ማሳወቁን ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቧል።