ትራምፕ ዩክሬን የአሜሪካን ሚሳይል ተጠቅማ ሩሲያ ውስጥ ዘልቃ ማጥቃቷን ተቹ
ትራምፕ በዩክሬን ጦርነት ዙሪያ ያለውን የአሜሪካ ፖሊሲ ሊቀይሩ እንደሚችሉ አመላክተዋል

የሩሲያ ቤተመንግስት ክሬሚሊን ትራምፕ ትችት መሰንዘራቸውን አድንቋል
ትራምፕ ዩክሬን የአሜሪካን ሚሳይል ተጠቅማ ሩሲያ ውስጥ ዘልቃ ማጥቃቷን ተቹ።
ተመራጩ የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከታይም መጽሄት ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ዩክሬን አሜሪካ የሰጠታችን ሚሳይል ተጠቅማ ሩሲያ ውስጥ ዘልቃ ጥቃት መፈጸሟን የተቹ ሲሆን የሩሲያ ቤተመንግስት ክሬሚሊን ይህን የትራምፕ አስተያየት አድንቋል።
ትራምፕ በዩክሬን ጦርነት ዙሪያ ያለውን የአሜሪካ ፖሊሲ ሊቀይሩ እንደሚችሉ አመላክተዋል።
"እየተካሄደ ያለው ነገር እብደት ነው። እብደት ነው። ሚሳይሎችን በመቶዎች በሚቆጠሩ ኪሎሜትሮች ሩሲያ ውስጥ ማስወንጨፍ በጽኑ እቃወማለሁ። ያንን የምናደርገው ለምንድን ነው? ይህን ጦርነት እያባባስነው ነው፤ ያ እንዲሆን መፈቀድ አልነበረበትም" ሲሉ ትራምፕ የአመቱ ምርጥ ሰው ሲል ለሰየማቸው መጽሄት ተናግረዋል።
ፕሬዝደንት ባይደን ባለፈው ወር ዩክሬን አሜሪካ ሰራሽ የሆኑ የረጅም ርቀት ሚሳይሎችን እንድትጠቀም በመፍቀድ፣ የዩክሬን ኃይሎችን የሩሲያን ጥቃት የመቋቋም አቅማቸውን ይጨምራል ያሉትን የመጨረሻ ሙከራ አድርገዋል።
ባይደን ያንን ውሳኔ ያሳለፉት ፕሬዝደንት ዘለንስኪ በተደጋጋሚ ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ ነበር።
የፕሬዝደንት ባይደን ጽ/ቤት ኃይት ሀውስ ባይደን ሀሳባቸውን የቀየሩት ሩሲያ 15ሺ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮችን ወደ ግንባር በማስጠጋቷ ምክያት መሆኑን ጠቅሷል። ትራምፕ ሶስት አመት ገደማ ያስቆጠረውን ጦርነት በፍጥነት ለማስቆም የሚያስችል እቅድ እንዳላቸውና በዝርዝር መናገር እንደማይፈልጉ ተናግረዋል። ትራምፕ ለመጽሄቱ "ጥሩ እቅድ አለኝ"፣ ነገርግን አሁን ከተናገርኩት "ትርጉም አልባ እቅድ ይሆናል" ብለዋል።
ዩክሬንን ሊተዋት እንደሆነ የተጠየቁት ትራምፕ "ስምምነት እንዲደረግ እፈልጋለሁ፤ ስምምነት ለመድረስ ደግሞ አንዱን አለመተው ያስፈልጋል" ሲሉ መልሰዋል።
ትራምፕ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ተሳትፎ ጉዳዩን የሚያባብሰው ነው ብለዋል።
በመጭው ጥቅምት 20 በዓለ ሲመታቸውን የሚያከናውኑት ትራምፕ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ከዘለንስኪ እና ከፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር በፓሪስ ተገናኝተዋል።
የትራምፕ ጦርነቱን በፍጥነት አስቆመዋለሁ የሚለው አቋም ሩሲያ ጋር ይቀራረባል የምትለው ካቭ ስጋት አድሮባታል።
ሮይተርስ ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው ዘለንስኪ ከሩሲያ ጋር ያለውን ጦርነት ለማስቆም በሚደረገው ድርድር የደህንነት ዋስትና እንዲሰጣት ለመጠየቅ ስብሰባውን ተጠቅመውበታል። ዘለንስኪ ዩክሬን የኔቶ አባል እንድትሆን ይፈልጋሉ።
ለሚቀርበው የሰላም እቅድ ዩክሬን ፍቃደኛ ባትሆን የጦር መሳሪያ ድጋፉን ያቆሙ እንደሆነ የተጠየቁት ትራምፕ "ጠቃሚ የሰላም እቅድ አለኝ ብየ አስባለሁ፤ ነገርግን አሁን ይፋ ካደረኩት ዋጋ የሌለው እቅድ ይሆናል"ብለዋል።
ክሬሚሊን ዩክሬን የረጅም ርቀት ሚሳይል ተጠቅማ ሩሲያ ውስጥ ጥቃት መፈጸሟን መተቸታቸውን እንደሚያደንቅ ገልጾ፣ የአውሮፓ ወታደሮችን ስለመላክ የሚደረገው ንግግር ግን ወደፊት ሊኖር የሚችልን ሰላም እውን እንዳይሆን የሚያደርግ ነው ብሏል።
ክሬሚሊን ቃል አቀባይ የትራምፕ ንግግር ከሩሲያ አቋም ጋር የሚመሳሰል ነው ብለዋል።
የሩሲያ ኃይሎች ጦርነቱ ከተጀመረ የመጀመሪያ ቀናት ወዲህ በከፍተኛ ፍጥነት እየገሰገሱ በመሆናቸው ጦርነቱ ምዕራባውያን እና የሩሲያ ባለስልጣናት ከባድ እና የመጨመረሻ ወደሚሉት ምዕራፍ እየገባ ነው።
ዩክሬን የአሜሪካ እና የእንግሊዝ ሚሳይሎችን ተጠቅማ ጥቃት ማድረሷን ተከትሎ ሩሲያ ኦሬሽኒክ በተባለ አዲስ ሚሳይል የአጸፋ ምለሽ ሰጥታለች።
ተጨማሪ የአየር መከላከያ ስርአት ወደ ዩክሬን እየተጓጓዙ መሆናቸውን የገለጸችው ዋሽንግተን ለዩክሬን የ988 ሚሊዮን ዶላር ወታደራዊ ድጋፍ እቅድ ይፋ አድርጋለች።