
ሀገር እየመሩ በሚገኙት ወቅት የሌላ ሀገር ዜግነት መቀበላቸው በአርጄንቲናውያን ዘንድ ቁጣን ቀስቅሷል
የአርጄንቲናው ፕሬዝዳንት ሃቪየር ማይሊ የጣሊያን ዜግነት ማግኝታቸው መነጋገርያ ሆኗል፡፡
በሮም ይፋዊ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት ፕሬዝዳንት ከጣልያን የሚነሳ የዘር ሀረግ አላቸው በሚል ነው እውቅናውን ያገኙት፡፡
ፕሬዝዳንቱ በሮም የሚገኙት “የጣሊያን ወንድሞች” በተሰኝ የሀገሪቱ ወዳጆች በሚሰባሰቡበት አመታዊ ድግስ ላይ ለመታደም ነው፡፡
ያልተለመደ በሚመስለው የጣሊያን ዜግነት አሰጣጥ ሂደት አንድ ሰው በአያቱ ወይም በቅድመ አያቱ የጣሊያናዊ ደም ካለበት ዜግነት እንዲያገኝ ይደረጋል፡፡
በአንጻሩ ከስደተኞች የተወለዱ ህጻናት የሀገሪቱን ዜግነት ለማግኝት 18 አመት መጠበቅ ይገደዳሉ፡፡
ይህን ህግ ቀለል ለማድረግ የስደተኛ ደጋፊዎች ህዝበ ውሳኔ እንዲደረግ በተደጋጋሚ ቢጠይቁም ቀኝ ዘመሙ የጆርጂያ ሜሎኒ አስተዳደር የስደተኛ ህጎችን ጠበቅ ማድረጉን ቀጥሏል፡፡
በዚህም በአስተዳደሩ ላይ በፖለቲከኞች እና በማህበረሰብ አንቂዎች ዘንድ ቁጣን የቀሰቀሰ ሲሆን በተመሳሳይ አርጄንቲናውያንም ለመሪያቸው በተሰጠው የውጭ ሀገር ዜግነት ላይ ቁጣቸውን እየገለጹ ነው፡፡
ሀቪየር ማይሊ ቀደም ሲል በየካቲት ወር በጣሊያን በነበራቸው ጉብኝት አድርገውት በነበረው ቃለ መጠይቅ አያተቶቹ ጣሊያናዊ እንደነበሩ 75 በመቶ ጣሊያናዊነት እንደሚሰማቸው መናገራቸው ይታወሳል፡፡
በማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ቁጣቸውን እየገለጹ የሚገኙ አርጄንቲናውያን ፕሬዝዳንታቸው “ይህን ያህል ጣሊያናዊነታቸው የሚያሳስባቸው ከሆነ በሮም ምርጫ ይወዳደሩ” በሚል እያፌዙ ይገኛሉ፡፡
ሌሎች ደግሞ በሌላ ሀገር ስልጣን መንበር ላይ የሚገኝ ፕሬዝዳንት የውጭ ሀገር ዜግነት መቀበል ፍጹም ከሉዐላዊነት እና አስተዳደር ነጻነት ጋር የሚጋጭ ነው በሚል ጉዳዩን እየተቹ ይገኛሉ፡፡
ወግ አጥባቂዋ የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሚሎኒ እና የአርጄንቲናው ፕሬዝዳንት ሀቭየር ማይሊ ባለፈው ወር በቦነስ አይረስ ከተገናኙ በኋላ የጠበቀ ግንኙነት መመስረታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡