ሄዝቦላህ እስራኤል በሊባኖስ ላይ የምታደርገውን ማንኛውንም ወረራ ለመመከት ዝግጁ መሆኑን አስታወቀ
የቡድኑ ምክትል መሪ ተዋጊዎቻችን እስራኤል በእግረኛ ጦር ልትፈጽመው የምትችለውን ጥቃት ለመመከት ዝግጁ ናቸው ብለዋል
በርካታ ቁጥር ያላቸው የእስራኤል ታንኮች በሊባኖስ ድንበር አቅራቢያ እየተሰባሰቡ እንደሚገኝ መገናኛ ብዙሀን እየዘገቡ ነው
የሄዝቦላህ ምክትል መሪ ሼክ ናይም ቃሲም እስራኤል በሊባኖስ ልትፈጽመው የምትችለውን የእግረኛ ጦር ጥቃት ለመመከት መዘጋጀታቸውን ተናገሩ፡፡
ምክትል መሪው ሀሰን ናስረላህ ከተገደሉ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ በቴሌቪዝን ቀርበው ባስተላለፉት መልዕክት ተዋጊዎቻችን “ወራሪዎችን” ለመከላከል በተጠንቀቅ ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በእስራኤል ላይ እየፈጸምነው ያለነው ጥቃት በዝቅተኛው አቅማችን ነው ያሉት መሪው ጥቃቱ እንደሚቀጥል እና በሁለቱ አካላት መካከል ያለው ውግያ ለረጅም ጊዜ ሊዘልቅ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል፡፡
ከድንበር አቅራቢያዎች 150 ኪሎሜትር ድረስ የሚምዘገዘጉ ሚሳኤል እና ሮኬቶችን እያስወነጨፈ የሚገኝው ቡድኑ የእስራኤል ጦር የሊባኖስን ድንበር ጥሶ የሚገባ ከሆነ በሙሉ አቅማችን እንዋጋለን ሲል ዝቷል፡፡
በተጨማሪም ባሳለፍነው አርብ የተገደሉትን የቡድኑን መሪ ሀሰን ናስረላህን የሚተካ ሰው በቅርቡ እንደሚያሳውቁ ነው የተናገሩት፡፡
የሊባኖስ ጠቅላይ ሚንስትር ናጂብ ሚካቲ በበኩላቸው ሁሉን አቀፍ ጦርነትን ለማስቆም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቀረበውን የሄዝቦላህን ተዋጊዎች የድንበር አካባቢ እንቅስቃሴ የሚገድበውን የውሳኔ ሀሳብ ለመተግበር ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
በደቡባዊ ሊታኒ ወንዝ አቅራቢያ ከሚገኝው ስፍራ የቡድኑ ተዋጊዎቹ እንዲለቁ በማድረግ የሊባኖስ ጦር በሀገሪቱ ደቡባዊ ድንበር 30 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ካለው ከወንዙ በስተደቡብ እንደሚያሰማራ ነው የተናገሩት፡፡
በዋና ከተማዋ ቤሩት እና በሌሎችም የሊባኖስ አካባቢዎች የአየር ጥቃቷን አጠናክራ የቀጠለችው ቴልአቪቭ ውጥረቱን ለማርገብ ወደ ኋላ የምትል አትመስልም፡፡
እስካሁን ጦሯን ድንበር አሻግራ ባታስገባም ከሊባኖስ ጋር በሚያዋስናት በሀገሪቱ ሰሜናዊ ድንበር አቅራቢያ ከፍተኛ ወታደራዊ እንቅስቃሴ እየታየ እንደሚገኝ ሮይተርስ አስነብቧል፡፡
በስፍራው በርካታ የእስራኤል ታንኮች በመሰባሰብ ላይ እንደሚገኙ እንዲሁም ተጠባባቂ ጦሯን በአካባቢው ማከማቸቷን የጠቀሰው ዘገባው ጦሩ የሄዝቦላህ ጠንካራ ይዞታ ናቸው በሚባሉ አካባቢዎች ላይ በቅርቡ የምድር ጥቃት ሊፈጽም የሚችልበት እድል ከፍተኛ ነው ብሏል፡፡
ዛሬ ጠዋት ላይ ወደ ድንበሩ ያቀኑት የመከላከያ ሚንስትሩ ዮቭ ጋላንት በዚህ አመት በድንበር አቅራቢያ ከሚገኙ መኖሪያቸው የተፈናቀሉ 60 ሺህ ዜጎችን ወደ ቤታቸው እንመልሳለን ብለዋል፡፡
ይህን ለማድረግ በእጃችን ላይ የሚገኝ የምድር ፣ የባህር እና የአየር ሀይላችን ሙሉ ለሙሉ እንጠቀማለን ሲሉ መዛታቸው ተዘግቧል፡፡