ዜጎቻቸውን ከሊባኖስ ለማስወጣት ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ የሚገኙ ሀገራት እነማን ናቸው?
በሄዝቦላህና እስራኤል መካከል የሚገኘው ውጥረት ወደ ከፍተኛ ደረጃ መሻገሩን ተከትሎ ሀገራት ለዜጎቻቸው የተለያዩ ማስጠንቀቂያዎችን ሲሰጡ ሰንብተዋል
የኢትዮጵያ በተለይም በደቡብ እና በምስራቅ የሊባኖስ አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎች አድራሻቸውን እንዲያስመዘግቡ ጥሪ አቅርባለች
በመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና ከጋዛው ጦርነት ቀጥሎ ከፍተኛ የስጋት ምንጭ የሆነው የሄዝቦላህ እና የእስራኤል ፍጥጫ ወደ ለየለት ጦርነት እየተንደረደረ እንደሚገኝ እየተነገ ነው፡፡
በሊባኖስ የመገናኛ መሳርያዎች ላይ የተገጠሙ ፈንጂዎችን በማፈንዳት ጥቃት ማድረስ የጀመረችው ቴልአቪቭ ከሰኞ ጀምሮ መጠኑ ከፍ ያለ የአየር እና የሚሳኤል ጥቃት በቤሩት ላይ እየፈጸመች ትገኛለች፡፡
ሄዝቦላህ ለእስራኤል እየሰጠ በሚገኝው ምላሽ እስከዛሬ በቡድኑ ጥቅም ላይ ውለው የማያውቁ ባላስቲክ ሚሳኤሎችን ጭምር በመጠቀም በማዕከላዊ እስራኤል ጥቃት እየፈጸመ ይገኛል፡፡
ይህን ተከትሎም ቀጠናው ከአስርተ አመታት ወዲህ ወደ አከባቢያዊ ጦርነት የማምራት እድሉ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ በመሆኑ አለም አቀፉ ማህበረሰብ እና ምዕራባውያን ሁለቱ ወገኖች ውጥረቱን እንዲያረግቡ ተደጋጋሚ ጥሪ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
በዛሬው እለት አሜሪካ እና አጋሮቿ በሄዝቦላህ እና እስራኤል መካከል የ21 ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ያቀረቡትን ጥያቄ የኔታንያሁ መንግስት ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡
ከዚህ ባለፈም የሀገሪቱ ጦር ኢታማዦር ሹም በሊባኖስ የምድር ላይ ጥቃት ለመፈጸም የሀገሪቱ ጦር እንዲዘጋጅ ትእዛዝ ማስተላለፋቸው ተሰምቷል፡፡
ኢታማዦር ሹሙ ሄርዚ ሃሊቪ በሰሜናዊ የሀገሪቱ ድንበር ተገኝተው በአካባቢው ለሚገኙ የጦር አባላት ባደረጉት ንግግር የአየር ሀይሉ እየፈጸመ ያለው ጥቃት ለእግረኛ ጦሩ መደላደሎችን ለመፍጠር ነው ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
በአካባቢው እያየለ ከሚገኝው ውጥረት ጋር በተገናኝ ሀገራት ዜጎቻቸውን ከሊባኖስ ለማስወጣት በጥድፍያ ውስጥ ይገኛሉ፡፡
ለመከከለኛው ምስራቅ በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኝው የአውሮፓ ህብረት አባሏ ቆጵሮስ ከቤሩት ያላት ርቀት በባህር የ10 ሰአት ጉዞ በአውሮፕላን ደግሞ የ40 ደቂቃ በረራ ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡
ቆጵሮስ በተመሳሳይ በ2006 በሄዝቦላህ እና እስራኤል መከከል በነበረው ጦርነት 60 ሺህ የውጭ ሀገራት ዜጎችን ለማስወጣት በማዕከልነት አገልግላለች፡፡
በአሁኑ ወቅት በሊባኖስ በርካታ ዜጎች ካሏቸው ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው አውስትራሊያ 15 ሺህ ዜጎቿን የቤሩት አየር መንገድ ከመዘጋቱ በፊት በአውሮፕላን ለማስወጣት እየሰራች ተገኛለች፡፡
ዜጎች ሀገሪቷን ለቀው ከመውጣታቸው በፊት ጦርነቱ የሚጀመር ከሆነ አንድ ሺህ ዜጎቿ በሊባኖስ የሚገኙት ካናዳ ከአውስትራሊያ ጋር በመተባበር በባህር ዜጎቻቸውን ለማስወጣት ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡
በቆጵሮስ ደሴት ሁለት ወታደራዊ ካምፖች ያሏት ብሪታንያ በበኩሏ በስፍራው የሚገኙ ሁለት የሮያል ኔቪ መርከቦቿን ዜጎቿን ከአካባቢው ለማስወጣት ጥቅም ላይ ለማዋል ያቀደች ሲሆን ሂደቱን ለማገዝ 700 ወታደሮቿን ወደ አካባቢው ልካለች፡፡
በተመሳሳይ አሜሪካ ዜጎቿን ከሀገሪቷ ለማስወጣት ወታደሮቿን ወደ ቆፕሮስ ስታሰማራ ፖርቹጋል በበኩሏ ከአውሮፓ ህብረት አጋሮቿ ጋር በመሆን እየተንቀሳቀሰች እንደምትገኝ አስታውቃለች፡፡
በቤሩት የኢትዮጵያ ቆንስላ ጄኔራል ጽሕፈት ቤት ባወጣው መረጃ በተለይም በደቡብ እና በምስራቅ የሊባኖስ አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎች አድራሻቸውን እንዲያስመዘግቡ ጥሪ አቅርቧል፡፡