የአረቡን አለም ለሁለት የከፈለው የሄዝቦላህ መሪ ግድያ
ለ32 አመታት ሄዝቦላህን የመራው ሀሰን ናስረላህ ከእስራኤል ባለፈ በአረቡ አለም ጠላቶችን አፍርቷል
ሳኡዲ አረብያ፣ ኳታር እና ባህሬን በግድያው ዙርያ ምንም አይነት ሀሳብ ካልሰነዘሩት መካከል ይጠቀሳሉ
የሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህ መሪ ሰይድ ሀሰን ናሰርላህ ባሳለፍነው አርብ በእስራኤል ጥቃት መገደሉን ተከትሎ በቀጠናው አዳዲስ ነገሮች በፍጥነት እየተከሰቱ ይገኛሉ።
አሜሪካ “የናስረላህ ግድያ እስከዛሬ ላጠፋቸው ጥፋቶች ተመጣጣኝ ነው” ስትል ሌሎች ምዕራባውያን ደግሞ ግድያው ሊያቀጣጥለው የሚችለውን ግጭት ፍራቻ ስጋታቸውን በመግለጽ ላይ ይገኛሉ።
የመካከለኛው ምስራቅ እና የአረቡ አለም ሀገራት በበኩላቸው ከናስረላህ ሞት ጋር በተገናኝ ሁለት አይነት ስሜት በማንጸባረቅ ላይ ናቸው።
በቀጠናው የተለያዩ ሀገራት እና በአረብ ሊግ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2016 በሽብርተኝነት ተፈርጆ የነበረው ሄዝቦላህ ፍረጃው የተነሳለት በዚህ አመት ነበር።
ሳኡዲ አረብያን ጨምሮ የሱኒ እስልምና ተከታይ ሀገራት በጉዳዩ ላይ ምንም አይነት ሀሳብ ከማንጸባረቅ ተቆጥበዋል።
ሳኡዲ አረብያ ዘግይታ እሁድ ባወጣችው መግለጫ በአካባቢው ያለውን ሁኔታ እየተከታተለች እንደምትገኝ ገልጻ የሊባኖስ ሉአላዊነት እንዲከበር ጥሪ ያቀረበች ሲሆን በመግለጫው ስለ ናስረላህ ግድያ ምንም ያለችው ነገር የለም።
በተመሳሳይ የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አል ሲሲ ከሊባኖስ ጠቅላይ ሚንስትር ናጂብ ሚካቲ ጋር በስልክ ባደረጉት ውይይት ግድያውን ሳያነሱ አልፈዋል።
ባለፉት ዓመታት ኢራን እና በአካባቢው የምትደግፋቸው ታጣቂ ቡድኖችን ከሚቃወሙት መካከል አንዷ ሆና የዘለቀችው ካይሮ ከኢራን ጋር ያላት ግንኙነት ቀጥተኛ ያልሆነ ነው።
ሌሎች የቀጠናው የሱኒ እስልምና ተከታይ ሀገራት ኳታር ፣ ባህሬን ፣ እና ሌሎቹ በናስረላህ ግድያ ዙርያ ዝምታን ከመረጡ መካከል ይጠቀሳሉ።
በባህሬን የሄዝቦላህ መሪን ገድያ ተከትሎ ሀዘናቸውን ለመግለጽ የተሰባሰቡ ዜጎች በፖሊስ መታሰራቸውን የመንግስት ተቃዋሚ መገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል።
ኢራን የ5 ቀናት ብሄራዊ የሀዘን ቀን ስታውጅ፤ ኢራቅ እና ሶርያን የመሳሰሉ ሀገራት በበኩላቸው ለሶስት ቀናት የሚቆይ ብሔራዊ ሀዘን አውጀዋል።
ከዚህ ባለፈ በአረቡ አለም ማህበራዊ ትስስር ገጽ ተጠቃሚዎች ዘንድ ይሄው ሁለት የተቃርኖ ሀሳብ በሰፊው ተንጸባርቋል።
አንዳንዶች እስራኤል የሙስሊሙ አለምን ታላላቅ መሪዎች በከፍተኛ ሁኔታ እየጨረሰች ነው በሚል ድርጊቱን ሲያወግዙ፤ ሌሎች ደግሞ ሄዝቦላ በሶርያ ጦርነት ከኢራን እና ሩስያ ጎን ተሰልፎ የበሽር አላሳድ መንግስት እንዲዘልቅ በማድረጉ ናስረላህን ወቅሰውታል።
ኤክስ (ትዊተርን) ጨምሮ በተለያዩ ማህበራዊ ትስስር ገጾች እየተሳራጩ ከሚገኙ ጹሁፎች መካከል “ሄዝቦላህ እስራኤሎች ያላደረጉትን በደል በሶርያዎች ላይ ፈጽሟል” የሚል ጽሁፍ በብዙዎች መጋራቱን ሮይተርስ አስነብቧል።
በሌላ በኩል “ልዩነታችሁን ለጊዜው አስቀምጡት በቦምብ እየተደበደበች የምትገኝው የአረብ ሀገር ናት ይህን በማውገዝ ድምጽ ሁኑ” የሚሉ ለዘብተኞችም አልጠፉም።