የእጅ ስልካቸውን በቀን ከ20 ጊዜ በላይ መጠቀም በዘር ፍሬ መጠን ላይ ጉዳት እንደሚያደርስ ተመራማሪዎች ተናግረዋል
የእጅ ስልክን አብዝቶ መጠቀም የወንድ የዘር ፍሬ መጠንን እንደሚቀንስ ተገለጸ።
ባለፉት 50 ዓመታት የወንድ ዘር ፍሬ መጠን በግማሽ መቀነሱን ካወቁ በኋላ ተጨማሪ ምርምሮችን ሲያደርጉ ቆይተዋል።
በማንችስተር ዩንቨርሲቲ የባዮሎጂ፣ ሜዲሲን እና ጤና ተመራማሪዎች ይፋ በተደረገ ጥናት መሰረት የእጅ ስልክ ወይም ሞባይል ስልክ አብዝቶ መጠቀም ለወንድ የዘር ፍሬ ወይም ስፐርም መቀነስ ይዳርጋል ማለታቸውን ሲኤንኤን ዘግቧል።
እድሜያቸው ከ18 እስከ 22 በሆናቸው ወንዶች ላይ እና የእጅ ስልካቸውን በቀን 20 ጊዜ በሚጠቀሙ ሰዎች ላይ በተደረገ ጥናት የዘር ፍሬ መጠናቸው ቀንሶ ተገኝቷል።
በዚህ ጥናት መሰረት 21 በመቶ የዘር ፍሬ መጠናቸው ቀንሶ ተገኝቷል የተባለ ሲሆን በተለይም 2G እና 3G ስልኮችን የሚጠቀሙ ሰዎች የበለጠ ለጉዳት ተደርገዋል ተብሏል።
የእጅ ስልኮች ከፍተኛ የራዲዮ አክቲቭ ስላላቸው የወንድ የዘር ፍሬ መጠን እንዲቀንስ ምክንያት ሆነዋል ተብሏል።
የእጅ ስልካቸውን በቀን አምስት ጊዜ እና ከዛ በታች የሚጠቀሙ ወንዶች የወንድ የዘር ፍሬያቸው ከፍተኛ እንደሚሆን ተመራማሪዎቹ ገልጸዋል።
ወንዶች የዘር ፍሬ መጠናቸውን ለመጨመር የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ፣ አልኮል መጠናቸውን እንዲቀንሱ እና አመጋገባቸውን እንዲያስተካክሉም ተመራማሪዎቹ ምክር ሀሳባቸውን ለግሰዋል።
እንዲሁም ሰዎች ስልካቸውን ሲጠቀሙ በተቻለ መጠን የጽሁፍ መልዕክት እንዲያደርጉ አልያም ወደ ራስቅላቸው ሳያስጠጉ እንድ ወይም ላውድ ላይ አድርግው ቢጠቀሙ የተሻለ እንደሚሆንም ተገልጿል።