በዓለም አቀፍ ደረጃ የወንድ ብልት መጠን አሳሳቢ በሆነ ሁኔታ ጨምሯል- ተመራማሪዎች
በዓለምአቀፍ ደረጃ የብልት ቁመት መጠን በ24 በመቶ ጨምራል ተብሏል
ተመራማሪዎች ለብልት መጠን መጨመር የከባቢ አየር በኬሚካል መበከልን አንድ ምክንያት ያስቀምጣሉ
በዓለም አቀፍ ደረጃ የወንድ ብልት መጠን አሳሳቢ በሆነ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን ተመራማሪዎች ገለጹ።
ከሰው ልጆች የሰውነት አካል ውስጥ አንዱ የሆነው ብልት መጠን ጉዳይ የብዙዎችን ትኩረት ይስባል።
የብልት መጠን ጉዳይ በራሱ የሰው ልጆችን የፍቅር እና ቤተሰባዊ ህይወትን ሲያወሳስብም ይሰማል።
የአሜሪካው ስታንፎርድ ዩንቨርሲቲ ላለፉት 29 ዓመታት በወንድ ልጅ ብልት መጠን ዙሪያ ያጠናውን ጥናት ይፋ አድርጓል።
በዚህ ጥናት መሰረት በዓለም አቀፍ ደረጃ የወንድ ልጅ ብልት ባለፉት 29 ዓመታት መሰረት በ24 በመቶ ጨምሯል።
ተመራማሪዎቹ ከፈረንጆቹ 1942 ጀምሮ እስከ 2021 ድረስ 75 ጥናቶችን ያጠና ሲሆን ከ55 ሺህ በላይ ሰዎች በጥናቱ ተሳትፈዋል ተብሏል።
በዚህ ጥናት መሰረትም በዓለም አቀፍ ደረጃ የወንድ ልጅ ብልት አማካኝ መጠን ከ12 ሴንቲ ሜትር ወደ 15 ሴንቲ ሜትር አድጓል ተብሏል።
የዩንቨርሲቲው ተመራማሪ ዶ/ር ሚካኤል ኢስንበርግ የወንድ ልጅ ብልት መጠን እየጨመረ ያለበት ፍጥነት ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ዓለም አቀፍ አማካኝ የብልት መጠን በፍጥነት መጨመር የሰውን ልጅ የወሲብ እና ፍቅር ህይወትን ሊጎዳ እንደሚችል ተሙራማሪው አሳስበዋል።
ተመራማሪዎቹ የወንድ ልጅ ብልት መጠን በየጊዜው እየቀነሰ ሊሄድ እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠው የነበረ ቢሆንም ውጤቱ ግን በተቃራኒው ሊሆን መቻሉን ዩሮ ኒውስ ዘግቧል።
ጎጂ ኬሚካሎች ወደ ከባቢ አየር መለቀቅ እና የአየር ንብረት ለውጥ መኖር ለወንድ ልጅ ብልት መጠን መጨመር ዋነኞቹ ምክንያቶች እንደሆኑ ተመራማሪዎቹ ተናግረዋል።
በተቃራኒው እነዚህ ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቁ ኬሚካሎች የወንድ የዘር ፍሬ ወይም ስፐርም መጠን እንዲቀንስ አድርገዋልም ተብሏል።