ሆቴሉ የስራ መቀዛቀዝን ጨምሮ ባጋጠሙት ሌሎች ችግሮች ምክንያት ስራ ለማቆም መገደዱን ነው ያስታወቀው
ያለፉትን 53 ዓመታት የናይሮቢ ድምቀት ሆኖ ያሳለፈው ሂልተን ሆቴል ስራ ሊቆም ነው፡፡
ሆቴሌ ከመጪው ታህሳስ ጀምሮ በሮቹን እንደሚዘጋና ለጊዜው ቁጥራቸው ያልተገለጸ ሰራተኞቹን እንደሚያሰናብትና ወደ ሌሎች በከተማዋ ወደሚገኙ ቅርጫፍ ይዞታዎቹ እንደሚያዛውር አስታውቋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ ባጋጠመው የስራ መቀዛቀዝ ምክንያት በኬንያ የቱሪስት መዳረሻ የነበሩና ጥቂት የማይባሉ ቅንጡ ሆቴሎች ስራ እያቆሙ መሆኑ ይነገራል፡፡
ከነዚህ መካከል ያለፉትን 53 ዓመታት የናይሮቢ ድምቀት ሆኖም ያገለገለው ሒልተን አንዱ ነው፡፡ ሆኖም የመዘጋቱ ምክንያት የወረርሽኙ ተጽዕኖ ብቻ እንዳልሆነ ገልጿል፡፡
እንደ ተነባቢው የሃገሪቱ ጋዜጣ ኔሽን ዘገባ ከሆነ 40 ነጥብ 57 በመቶው የሆቴሉ የአክስዮን ድርሻ በኬንያ መንግስት የተያዘ ነው፡፡
ያጋጠሙ ችግሮችን በተመለከተ ከሆቴሉ ባለቤቶች ጋር ሰፊ ውይይቶች መደረጋቸውን የተናገሩት የሆቴሉ ቃል አቀባይ ከፈረንጆቹ ታህሳስ 31 ቀን 2022 ጀምሮ የሒልተን ናይሮቢ በር ለመጨረሻ ጊዜ ይዘጋና ስራ ያቆማል ብለዋል፡፡
ከጥቂት ዓመታት በፊት በሰማይ ጠቀስነት ከሚጠቀሱና በናይሮቢ እምብርት ከሚገኙ ህንጻዎች መካከል አንዱ በፈረንጆቹ 1969 የተገነባውና 287 ክፍሎች ያሉት ሒልተን ሆቴል ነበር፡፡
ኬንያ ከአሁን ቀደምም መሰል የእውቅ ሆቴሎች መዘጋት አጋጥሟታል፡፡ ናይሮቢ ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ልክ ወረርሽኙ ባጋጠመ በአምስት ወራት ውስጥ ነበር የተዘጋው፡፡
የአሁሩ ኬንያታ መንግስት በሆቴል አስተዳደር ድርጅቱ በኩል የናይሮቢ ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል የ33 ነጥብ 83 ድርሻ ባለቤት ነበርም ተብሏል፡፡