የኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በኡሁሩ ኬንያታ የቀረበለትን የህገ መንግስት ማሻሻያ ውድቅ አደረገ
በማሻሻያ ሃሳቡ ላይ የመጨረሻ ያለውን ውሳኔ ዛሬ ሃሙስ ሰጥቷል
ፍርድ ቤቱ የ11 ዓመት እድሜ ያለውን የሃገሪቱን ህገ መንግስት ለማሻሻል “ድልድዩን እንገንባ” በሚል ስም የቀረበለትን ሃሳብ ውድቅ አድርጓል
የኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የቀረበለትን የህገ መንግስት ማሻሻያ ውድቅ አደረገ፡፡
ሰባት ዳኞች የተሰየሙበት ፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የጀመሩትን ህገ መንግስት የማሻሻል ሂደት ውድቅ በማድረግ ከአሁን ቀደም ያሳለፈውን ውሳኔ አጽንቷል፡፡
በችሎቱ ከተሰየሙት ከሰባቱ ዳኞች ሶስቱ ህገ መንግስቱን በማሻሻሉ ሃሳብ ኬንያታ ተነሳሽነቱን ወስደዋል በሚል ተከራክረዋል፡፡ ሁለት ዳኞች አልወሰዱም በሚል ሲሞግቱ ቀሪዎቹ ሁለቱ ደግሞ ድምጸ ተዓቅቦን መርጠዋል፡፡ በጥቅሉ ከሰባቱ ዳኞች ስድስቱ ፕሬዝዳንቱ የህገ መንግስት ለውጥ ጥያቄውን ሊያንቀሳቅሱም ሆነ ሊመሩ አይችሉም ሲሉ ወስነዋል፡፡
ቢውልዲንግ ብሪጅ ኢንሼቲቭ (BBI) በሚል የቀረበው የማሻሻያ ሃሳብ ኢ-ህገመንግስታዊ ነው ሲሉም ነው ዳኞቹ ያስቀመጡት፡፡
ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ባሳለፍነው ግንቦትም ውጥኑን ውድቅ አድርጎ ነበር፡፡ ፕሬዝዳንቱ በማን ፈቃድ የማይመለከታቸውን ሂደት እንደጀመሩት በመጠየቅም በህግ ሊጠየቁ እንደሚችሉ አሳስቦም ነበር በወቅቱ፡፡
ሆኖም ኬንያታ ከምርጫ በኋላ የሚያጋጥመውን ደም መፋሰስ ከማስቀረት ባሻገር አካታች የፖለቲካ አውድን ለመፍጠር ያስችላል በሚል ተከራክረዋል፡፡
ማሻሻያው አስፈጻሚው የመንግስት አካል በአዲስ መልክ እንዲዋቀር የሚያጠይቅ ነው፡፡ የሃገሪቱ ፓርላማ አባላት ወይም የፓርላማው ወንበር ቁጥር ከ290 ወደ 360 ከፍ እንዲልም ሃሳብ ያቀርባል፡፡
ነገር ግን ማሻሻያው በፕሬዝዳንቱ ለሚመራው የሃገሪቱ የአስፈጻሚ አካል የበለጠ ስልጣን የሚሰጥ ነው በሚል ተተችቷል፡፡ ኡሁሩ ራሳቸውን የበለጠ በስልጣን ኮርቻ ላይ ለማደላደል ያደረጉት ነው በሚል በምክትላቸው በዊሊያም ሩቶ ሳይቀር ተተችተዋል፡፡
ሩቶ በ2017ቱ የኬንያ ምርጫ ነበር በራሳቸው በኡሁሩ ኬንያታ አቅራቢነት ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው የተሾሙት፡፡ ነገር ግን ይህ በሆነ በዓመቱ ኬንያታ ከቀዳሚ የፖለቲካ ተቀናቃኛቸው ከ77 ዓመቱ አዛውንት ራይላ ኦዲንጋ ጋር አዲስ የአጋርነት ስምምነትን ፈጽመዋል፡፡ የሃገሪቱን ህገ መንግስት የማሻሻል ሂደቱም ከዛን ወዲህ የተጀመረ ነው፡፡ ይህ ሩቶን አላስደሰተም፡፡
ስምምነቱና የማሻሻያው ሂደት መጀመር ራይላ በፕሬዝዳንትነት የሚመረጡ ከሆነ በስምምነቱ መሰረት ኡሁሩ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ ለመያዝ እንዳሰቡ የሚያሳይ ነው የሚሉ ጭምጭምታዎችም ነበሩ፡፡
የ60 ዓመቱ ኬንያታ ከወር በፊት የራይላ ኦዲንጋን ፕሬዝዳንታዊ እጩነት መደገፋቸው የሚታወስ ነው፡፡
የራይላን ድጋፍ ያገኘው የኡሁሩ ጥረት በፍርድ ቤቱ ተቀባይነትን ቢያገኝ ኖሮ በመጪው ነሃሴ ከሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በኋላ ህገ መንግስቱን ያሻሽሉ ነበር፡፡ ሆኖም ፍርድ ቤቱ 4 ዓመታት ያስቆጠረውን ጉዳይ ውድቅ አድርጓል፡፡ ይህም ዊሊያም ሩቶን መሰል ፖለቲከኞችን ጨምሮ ውጥኑን ለተቃወሙ ሁሉ ትልቅ ነገር እንደሆነ ነው የተነገረው፡፡
የኬንያ ህገ መንግስት ለመጨረሻ ጊዜ የተሻሻላ በፈረንጆቹ 2010 ነበር፡፡