የኢትዮጵያና የሱዳን የድንበር ውዝግብ ታሪካዊ ዳራ ምን ይመስላል?
የኢትዮጵያ እና የሱዳን ድንበር ከፍተኛ የጋራ የፖለቲካ ኮሚቴ ዛሬ በካርቱም ስብሰባውን ጀምሯል፡፡ ስብሰባው የሚካሔደው ለረዥም ዓመታት የዘለቀው የሁለቱ ሀገራት የድንበር ውዝግብ ውጥረቱ ባየለበት ወቅት ነው፡፡
ባለፉት ጥቂት ቀናት ሱዳን በድንበር አካባቢ ከፍተኛ ጦር ያሰለፈች ሲሆን በኢትዮጵያ ተይዞብኛል የምትለውን መሬት በኃይል ማስመለሷን እና ከኢትዮጵያ ጋር በሚያወዛግባት ስፍራ ላይ ሉዓላዊነቷን ማረጋገጧን አውጃለች፡፡
የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ም/ቤት ሊቀመንበር አብዱልፈታ አልቡርሃን ድንበር አካባቢ የሰፈረውን የሀገሪቱን ጦር ጎብኝተዋል፡፡
አልቡርሃን ድንበር አካባቢ ተገኝተው ወታደሮችን ሲጎበኙ
በድንበር ጉዳይ የትዮጵያ እና የሱዳን የመጨረሻው ስብሰባ ባለፈው ግንቦት በአዲስ አበባ የተካሄደ ሲሆን በሁለቱ ሀገራት ድንበር ላይ የተፈጠረው የፀጥታ ውጥረት ፣ የጋራ የድንበር ኮሚቴው አሁን ላይ ስራ እንዲጀምር ምክንያት ሆኗል፡፡ ተመሳሳይ ስብሰባ ከአንድ ወር በኋላ ሊካሄድ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ በሁለቱ ሀገራት ውስጣዊ ችግሮች ምክንያት ተሰርዟል፡፡
የሱዳን ጦር ባለፈው ረቡዕ በሰጠው መግለጫ በፋሻቃ ግዛት “ጃባል አቡጢዩር” አካባቢ “የኢትዮጵያ ሚሊሻዎች” አደረሱብኝ ላለው ጥቃት ምላሽ መስጠቱን ካሳወቀ በኋላ በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል የድንበር ውጥረቱ እንደገና አይሏል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥትም እንዲሁ የሱዳን ጦር የተደራጀ ጥቃት በመፈጸም በርካታ ንጹሀንን መግደሉን እና ሌሎች ጉዳቶችን ማድረሱን በዛሬው ዕለት አስታውቋል፡፡
ሁለቱም ሀገራት በውስጣዊ የፖለቲካ አለመረጋጋት እና በለውጥ ጉዞ ላይ የሚገኙ ሲሆን የድንበር ጉዳዮችም አንዴ ከረር ሌላ ጊዜ ላላ የማለት ሁለት ገጽታን የተላበሱ ናቸው፡፡
የሱዳንና የኢትዮጵያ የድንበር ግጭት ሱዳን ከቅኝ ግዛት ከተላቀቀችበት ከ 1950 ዎቹ ጀምሮ የቆየ ረዥም ታሪክ ያለው ሲሆን በሁለቱ ሀገራት መካከል የድንበር ማካለል ስራ ቸል መባሉ ውጥረቶች እንደገና እንዲያገረሹ አድርጓል፡፡
በዚህ ጽሁፍ በካርቱም እና በአዲስ አበባ መካከል ያለው የድንበር ውዝግብ እንዲሁም ያለመግባባቱ ምንጭ የሆነውን የፋሻቃ ግዛት የድንበር ግጭት ተዳሷል፡፡
ሚሊሻዎች እና ፋሻቃ
በፋሻቃ ግዛት ውስጥ ላሉ ችግሮች እና የድንበር ግጭቶች ዋና ተዋናዮች ብዙውን ጊዜ የሱዳን ታጣቂዎች እና በአከባቢው የሚገኙ የኢትዮጵያ ሚሊሻዎች (በፌዴራል መንግሥት ስልጣን ስር ያልሆኑ) ሲሆኑ በአፈና ፣ በገንዘብ ጥያቄ ፣ በከብት ዘረፋ እና በእርሻ መሬቶች ወረራ ተግባራት ይታወቃሉ፡፡
ሱዳን ፋሻቃ አካባቢ ላይ ሉዓላዊነቷን ማረጋገጧን የገለጸች ሲሆን ከድንበር ማካለል ጋር በተያያዘ ካልሆነ በስተቀር በእነዚህ መሬቶች ላይ ከኢትዮጵያ ጋር ክርክር እንደሌለ ይፋ አድርጋለች፡፡
ካርቱም እንደምትለው ፣ ድንበሮችን የማካለሉ ጉዳይ የሱዳን ቅኝ ገዢ በነበረችው በብሪታንያ አማካኝነት እ.ኤ.አ. በ 1902 የተጀመረ ቢሆንም እስካሁን እልባት ማግኘት አልቻለም፡፡ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ድንበር እየጣሱ በመግባት የእርሻ ስራ ሲያከናውኑ ስለመቆየታቸውም ነው ሱዳን የምትገልጸው፡፡
“አል-ፋሻቃ” በመባል የሚታወቀው ግዛት በሁለቱ ሀገራት ድንበር ላይ የሚገኝ የእርሻ ቦታ ሲሆን በሦስት አካባቢዎች፡“አል-ፋሻቃ አል-ኩብራ” ፣ “አል-ፋሻቃ አል-ሳግራ” እና “ደቡብ ክልል” በሚል በ “ባሳላም” እና “አትባራ” ወንዞች ተከፍሏል። በነዚህ አካባቢዎች ፣ በተለይ በግብርና ስራ ወቅት እና ምርት ለመሰብሰብ ዝግጅት በሚደረግበት ወቅት ግጭቶች የተለመዱ ናቸው፡፡
የሱዳን ቅሬታ
እ.ኤ.አ በሰኔ 1995 አሁን በህይወት የሌሉትን የቀድሞ የግብፅ ፕሬዝዳንት ሆስኒ ሙባረክን ፣ አዲስ አበባ ላይ ለመግደል ከተደረገው ሙከራ ጋር በተያያዘ የሱዳን እና የኢትዮጵያ ግንኙነት በከፍተኛ ደረጃ ሻክሮ ነበር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከግድያ ሙከራው ጀርባ የሱዳን እጅ አለ የሚል ነው፡፡ ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ ጦር ወደ ግዛቴ ገብቷል በሚል ሱዳን በቀጣዩ ዓመት ፣በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የአመራር ዘመን ወቅት ፣ በ 1996 ለተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ም/ቤት አቤቱታ አቅርባለች፡፡
በቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ወቅትም የድንበር ግጭቶች የቀጠሉ ሲሆን የሁለቱ ሀገራት መንግሥታት በፋሻቃ ግዛት ላይ ያለውን አለመግባባት በመፍታት ፣ በፍጥነት ነገሮችን ለማረጋጋት በድንበር ጉዳይ ላይ የሚወያይ የጋራ የቴክኒክ ኮሚቴ እንዲቋቋም አድርገዋ፡፡ ይህ እርምጃ ግጭቶችን ከማስቆም አንጻር የተወሰነ አስተዋጽኦ ቢኖረውም እስካሁን ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት አልቻለም፡፡ ወሰን ለማካለል ስምምነት ከተደረሰ እ.ኤ.አ. ከ 2013 በኋላ የኮሚቴው ስራ ቆሟል፡፡
እ.ኤ.አ በ 2015 አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ዳግም ከተመረጡ በኋላ ግጭቱ የቆየ እና ጥናት የሚያስፈልገው መሆኑን ገልጸው ይህን ከግምት በማስገባት መንግሥታቸው ከሱዳን ጋር ያሉትን የድንበር ጉዳዮች በተመለከተ፣ ከህዝቡ ጋር ምክክር ሳይደረግ እና ያለ ህዝብ እውቅና ምንም ውሳኔ መወሰን እንደማይችል አስታውቀዋል፡፡
እ.ኤ.አ በ 2017 በኃይለማሪያም ደሳለኝ እና በሀሰን አልባሽር መንግሥታት መካከል በሁለቱ ሀገራት ድንበሮች ላይ ነፃ ቐጣናዎችን ለማቋቋም እንዲሁም የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ውህደት ለመፍጠር ስምምነት ተደረሰ፡፡
ይሁን እንጂ የፋሻቃ ግጭት መፍትሄ አላገኘም፡፡ በመሆኑም የሱዳን መንግስት ሱዳናውያን ለኢትዮጵያውያን መሬታቸውን እንዳያከራዩ የሚል ውሳኔ አሳለፈ፡፡
በነሐሴ 2018 ደግሞ ሱዳን እና ኢትዮጵያ ውጥረቶችን ለመቀነስ በሚል ፣ በድንበሮቻቸው ላይ ከሁለቱ ሀገራት የተውጣጣ ጥምር ጦር ለማስፈር ተስማሙ፡፡ አካባቢውን በጋራ ለማልማትም ስምምነት ተደርሶ ነበር፡፡
የቅርብ ጊዜያት ውጥረቶች
ከህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር እና ድንበሮችን በአግባቡ መቆጣጠር ካለመቻል ጋር በተያያዘ በሚሰነዘሩ ክሶች ምክንያት በ2019 እና በ2020 ፣ አዲስ አበባ እና ካርቱም አለመግባባታቸው እያየለ መጥቶ ተደጋጋሚ ውይይቶችን ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡
በለፈው ግንቦት ወር ደግሞ የድንበር ውጥረቱ አይሎ ተኩስ እስከመለዋወጥ ተደርሷል፡፡ በወቅቱ በነበረው የተኩስ ልውውጥ “የኢትዮጵያ መንግሥት ጦር ሚሊሻዎችን ሲደግፍ ነበር” በሚል ሱዳን ወቀሳ አሰምታለች፡፡
ከሳምንት በፊት ባለፈው ረቡዕ ደግሞ በኢትዮጵያ ሚሊሻዎች ጥቃት ተፈጽሞበት አጸፋዊ ምላሽ መስጠቱን የሱዳን ጦር አስታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ ምክትል ጠ/ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንም ዛሬ ታህሣሥ 13 ቀን 2013 ዓ/ም ካርቱም ላይ ባደረጉት ንግግር የሱዳን ጦር ካለፈው ጥቅምት 30 ጀምሮ በኢትዮጵያ ላይ በከባድ መሳሪያ የታገዘ የተቀናጀ ጥቃት ሲፈጽም መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ በጥቃቱም የሰዎች ህይወት ማለፉን እና የአርሶአደሮች ሰብል መዘረፉን አንስተዋል፡፡
የሁለቱ ሀገራት የአሁኑ ውጥረት ባለፉት 25 ዓመታት ከነበረው ሁሉ የላቀ ነው፡፡ ይሁንና የቆየው “የሀገራቱ ወዳጅነት በአሁኑ ክስተት አይቋረጥም” በሚል የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ውጥረቱን ሊያረግብ የሚችል መግለጫ አውጥተዋል፡፡
በዛሬው ዕለት የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ከፍተኛ የጋራ የፖለቲካ ኮሚቴ በጉዳዩ ዙሪያ ካርቱም ላይ የጀመረው ውይይት አንዳች ፋይዳ ያመጣ ይሆን? መልስ የሚያሻው ጥያቄ ነው፡፡