"በኢትዮጵያ እና ሱዳን ድንበር ላይ የሚፈጠሩ ክስተቶች የሁለቱን ሀገራት ትስስር አያቋርጡም" ጠ/ሚ ዐቢይ
ችግሩ በውይይት እንደሚፈታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል
በኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር የተፈጠረውን ክስተት መንግሥት በቅርብ እየተከታተለ መሆኑን ጠ/ሚ ዐቢይ ገለፁ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ "በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ላይ ከአከባቢው ሚሊሻዎች ጋር የተከሰተውን ክስተት መንግስቱ በቅርብ እየተከታተለ ነው" ብለዋል፡፡ "ችግሮችን ለመፍታት ሁሌም ውይይትን የምንጠቀም በመሆኑ እንደዚህ ያሉ ክስተቶች የሁለቱን ሀገራት ትስስር አያቋርጡም" ያሉም ሲሆን "አለመስማማትን የሚደግፉ አካላት የታሪካዊ ግንኙነታችንን ጥንካሬ በግልጽ አይረዱም" ሲሉም በትዊተር ገጻቸው ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሚሊሺያዎች ወደ ሱዳን ግዛት ገብተው ጥቃት እንደፈጸሙ የሱዳን መንግስት መግለፁን ተከትሎ ነው ጠ/ሚኒስትሩ ስለጉዳዩ የገለፁት።
የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ በሱዳን ወታደሮች እና “በኢትዮጵያ ሚሊሻዎች” መካከል በተፈጠረው ግጭት ላይ ያተኮረ መግለጫ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡ በመግለጫቸውም ማክሰኞ ታህሣሥ 6 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት ላይ የሱዳን ወታደሮች በ ‘ጃባል አቡጢዩር’ አካባቢ ቅኝት አድርገው ሲመለሱ “ወደ ሱዳን ግዛት ገብተው አድፍጠው በነበሩ የተወሰኑ የኢትዮጵያ ሚሊሺያዎች ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል” ብለዋል፡፡ በዚህም ጥቃት የሰዎች ህይወት መጥፋት እና የንብረት ጉዳት መድረሱን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል፡፡
የሱዳን ጦርም ከጠቅላይ ሚኒስትር ሃምዶክ አስቀድሞ ተመሳሳይ መግለጫ አውጥቷል።
ይህን ጉዳይ በተመለከተ ለአል ዐይን አማርኛ በስልክ አስተያየት የሰጡት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፣ በኢትዮጵያ እና በሱዳን ድንበር ላይ መሰል ግጭቶች ከዚህ ቀደምም እንደሚነሱ ተናግረዋል፡፡
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ በሱዳን ታጣቂዎች እና በኢትዮጵያ ሚሊሻዎች የተፈጠረውን ግጭት ጨምሮ በሁለቱ ሀገራት ድንበር ጉዳይ ላይ በከፍተኛ አመራሮች ደረጃ ውይይት በመደረግ ላይ መሆኑን አንስተዋል፡፡ ላለፉት ጊዜያትም ውይይት ሲደረግ መቆየቱንና በዚህም ዘላቂ እልባት ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን ነው አምባሳደር ዲና ያብራሩት፡፡
የኢትዮጵያ እና የሱዳን የጋራ የድንበር ኮሚሽን በሚቀጥለው ሳምንት ውይይት እንደሚያደርግ የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ተናግረዋል፡፡