የኢትዮ-ሱዳን ድንበር የጋራ ከፍተኛ የፖለቲካ ኮሚቴ ስብሰባ ዛሬና ነገ በካርቱም ይካሔዳል
ም/ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ሱዳን ገብተዋል
ድንበር የማካለል ስራን ስለማስጀመር የሱዳን እና የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ይመክራሉ
የኢትዮጵያ እና የሱዳን የጋራ የድንበር ጉዳይ ላይ ለመታደም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ ዛሬ ማለዳ ሱዳን ካርቱም ገብቷል፡፡ የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር ቀንዓ ያደታ (ዶ/ር) እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት አማካሪ ገዱ አንዳርጋቸውም በጉብኝቱ ተካተዋል፡፡
የልዑኩ አባላት ካርቱም አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የሱዳን የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር አምባሳደር ኦማር በሽር ማኒስ እና ሌሎች ባለስልጣናት አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
የሁለቱ ሀገረት ከፍተኛ ባለስልጣናት ለዓመታት በዘለቀው የድንበር ጉዳይ ላይ ለሁለት ቀናት ውይይት እንደሚያደርጉ ከሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አል ዐይን ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ ስምምነት በተደረሰባቸው እና ሁለቱ ሀገራት በተፈራረሙባቸው ማዕቀፎች አማካኝነት በድንበር ጉዳይ ላይ ትኩረት አድርገው የሚወያዩ ሲሆን ድንበር የማካለል ስራ ስለመጀመርም ይነጋገራሉ፡፡
የኢትዮ ሱዳን ድንበር የጋራ ከፍተኛ የፖለቲካ ኮሚቴ በግንቦት ወር በአዲስ አበባ ውይይት ያደረገ ሲሆን የአሁኑ ከአዲስ አበባው ውይይት የሚቀጥል ነው፡፡ በአዲስ አበባው ውይይት ሁለቱ ሀገራት የድንበር ጉዳዮችን ለመፍታት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ፣ በድንበር ላይ የሚፈጸሙ ህገወጥ ተግባራትን ለመከላከል እንዲሁም በድንበር ላይ የሚገኙ ዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ ተስማምተው ነበር፡፡
የካርቱሙ ስብሰባ በሰኔ ወር ይካሔዳል ተብሎ የነበረ ቢሆንም በሁለቱ ሀገራት ውስጣዊ ችግሮች የተነሳ ሳይካሔድ ቆይቶ እስከዛሬ ደርሷል፡፡
በኢትዮጵያ እና በሱዳን የድንበር ጉዳይ ከሰሞኑ ከፍተኛ ውጥረት ነግሷል፡፡