የኢትዮጵያ ሚሊሺያዎች ወደ ሱዳን ግዛት ገብተው ጥቃት እንደፈጸሙ የሱዳን ጦር ገለጸ
የሱዳን ጦር የኢትዮጵያ ሚሊሻዎች ፈጸሙ ባለው ጥቃት ዙሪያ መግለጫ አውጥቷል
ሚሊሺያዎቹ በፈጸሙት ጥቃት የሰዎች ሕይወት መጥፋቱ እና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ተገልጿል
የሱዳን ጦር ባወጣው መግለጫ የሀገሪቱ ታጣቂ ኃይሎች የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ እና በሱዳን ላይ የሚያስከትለውን መዘዝ በመከታተል ላይ እንደሚገኙ ገልጿል። እነዚህም የስደተኞች ወደ ሱዳን ግዛቶች መግባት እና በሁለቱ ሀገራት መካከል ባለው ድንበር ላይ ያለው አለመረጋጋት መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡ በዚህም የሀገሪቱ ታጣቂ ኃይል በርካታ እርምጃዎችን መውሰዱን ያነሳው መግለጫው በተለይም ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ወደ ሱዳን እንዲገቡ መፍቀድ እና ግብረሰናይ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው መተባበር ዋነኞቹ ስለመሆናቸው ጠቅሷል። በተጨማሪም ጦሩ በኢትዮጵያ በነበረው ውጊያ የፌዴራል መንግሥትም ይሁን የትግራይ ተዋጊዎች የሱዳንን መሬት እንዳይጠቀሙ ሲጠብቅ መቆየቱንም ገልጿል።
ይሁንና ትናንት ማክሰኞ ታህሣሥ 6 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት ላይ የኢትዮጵያ ሚሊሺያዎች ወደ ሱዳን ግዛት ገብተው ጥቃት እንደፈጸሙ የሱዳን ጦር ገልጿል።
ሚሊሺያዎቹ 'ጃባል አቡጢዩር' በተባለ አካባቢ አድብተው እንደፈጸሙት በተገለጸው ጥቃት የሰዎች ሕይወት መጥፋቱን እና በንብረትም ላይ ጉዳት መድረሱን መግለጫው ያትታል። የቆሰሉ ሰዎችም መኖራቸው ቢጠቀስም፣ ምን ያክል ሰዎች እንደተገደሉ እና እንደተጎዱ ግን አልተገለጸም።
ጥቃቱ በተፈጸመበት ወቅት በአካባቢው የነበሩ የሱዳን ታጣቂዎች እና ነዋሪዎች ለመከላከል ጥረት ማድረጋቸውን በመግለጽ ጦሩ ሀገሪቱን ከጥቃት እና ከወረራ ለመከላከል የገባውን ቃል እንደሚፈጽም አስታውቋል።
ከሰሞኑ በኢትዮጵያ እና ሱዳን ድንበር አካባቢ አለመረጋጋት ስለመኖሩ ጭምጭምታዎች ቢሰሙም ሁለቱም ሀገራት በይፋ ችግሮች ስለመኖራቸው ሳይገልጹ ቆይተዋል። በሱዳን በኩል በሀገሪቱ ጦር ምሽት ላይ ስለቀረበው ወቀሳ በኢትዮጵያ በኩል ወዲያው የተሰጠ ምላሽ የለም።
የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ባለፈው እሁድ በኢትዮጵያ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚነስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ከተነጋገሩባቸው ጉዳዮች አንዱ የድንበር ጉዳይ ነው።