በሶማሌ ክልል በተከሰተው ድርቅ ከ2.5 ሚልየን በላይ ዜጎች ላይ ጉዳት ማድረሱን የክልሉ መንግስተ አስታወቀ
በድርቁ ሳቢያ 250 ሺህ ገደማ እንሰሳት መሞታቸውንም ክልሉ ገልጿል
በሶማሌ ክልል ከሚገኙት 11 ዞኖች ውስጥ በዘጠኙ የድርቅ አደጋ ተከስቷል
በሶማሌ ክልል የክረምት ዝናብ በተፈለገው ደረጃ ባለመዝነቡ እና የብልጉም ዝናብ ሳይዘንብ በመቅረቱ ድርቅ መከሰቱን የክልሉ መንግስት አስታወቀ።
የሶማሌ ክልል የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ፈርሃን ጅብሪል ከአል ዐይን ኒውስ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ድርቁ በክልሉ ከሚገኙ 11 ዞኖች ውስጥ በዘጠኙ ዞኖች መከሰቱን ተናግረዋል።
በድርቁ ሳቢያ በዘጠኙ ዞን ውስጥ የሚገኙ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ገደማ ዜጎች ለጉዳት መዳረጋቸውንም አቶ ፈርሃ አስታውቀዋል።
እንዲሁም የክልሉ ህዝብ የጀርባ አጥንት የሆኑት እንሰሳት የድርቁ ሰለባ ሆነዋል ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ እስካሁንም ከ250 ሺህ ገደማ እንሰሳትም መሞታቸውን ገልፀዋል።
እስካሁን የጠፋ የሰው ህይወት የለም ያሉት አቶ ፈረሃ፤ “ነገር ግን የድርቁ ሁኔታ እና አስከፊነት ጊዜ የሚሰጥ አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል።
የሶማሌ ክልል መንግስት የድርቅ አደጋውን ተከትሎ የክልሉን ህዝቡንና እንሰሳትን ለመታደግ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን በማድረግ ላይ መሆኑን ያነሱት አቶ ፈረሃ፤ ባለፈው ህዳር ወር 200 ሚልየን ተጨማሪ በጀት መድቦ ወደ ስራ መግቱን አስታውሰዋል።
ከድርቁ ስፋት አኳያ የፀደቀው ተጨማሪ በጀት በቂ ባለመሆኑ መንግስት የካፒታል በጀትን ጨምሮ ባለው አቅም ሁሉ ለድርቁ ምላሽ በመስጠት ላይ መሆኑንም ገልፀዋል።
የክልሉ መንግሥት የተለያዩ ኮምቴዎችን በማዋቀር የእለ ተእለት እርዳታ በመስጠት ላይ መሆኑን ያስታወቁት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ ከነዚህም በየቀኑ ውሃን በቦቴ፣ አልሚ ምግቦችና ለእንሰሳት መኖ እስከ ቀበሌ እያደረሰ መሆኑን ለአብነት አንስተዋል።
ይህ እርዳታና ድጋፍ በቀጥታ ለህዝቡና ለታለመለት አላማ መዋሉ የሚከታተል በክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሁመድና ም/ር/ መስተዳድር አቶ ኢብራሂም ኡስማን የሚመሩ ኮሚቴዎችም በስራ ላይ መሆናቸውንም አስታወውቀዋል።
በክልሉ የተከሰተው ድርቅ እስከ ሚያዚያ ወር ድረስ ሊቆይ የሚችል መሆኑን ያነሱት አቶ ፈረሃ፤ ክልል ባለው አቀም በሙሉ ድርቁን ለመቋቋም እየሰራ እንሆነ ተናግረዋል
መላው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ባለሀብቱ፣ አቅሙ ያላቸው እና ድርጅቶች ከሶማሌ ክልል ህዝብ ጎን በመሆን ይህን ድርቅ ለመቀልበስ የበኩላቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።