በተያዘው ዓመት ብቻ 255 ሺህ ስደተኞች አውሮፓ ገብተዋል ተብሏል
የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ስደተኞችን በጋራ ለመቀበል ተስማሙ ፡፡
የአውሮፓ ህብረት በስደተኞች ዙሪያ የጋራ አቋም ለመያዝ ላለፉት ቀናት ሲወያይ ቆይቷል፡፡
የህብረቱ አባል ሀገራት ተወካዮች፣ የእንደራሴ ምክር ቤት አባላት እና ሌሎች ተቋማት ከሌሎች አህጉራት ወደ አውሮፓ በሚመጡ ስደተኞች ዙሪያ መወያየታቸው ተገልጿል፡፡
ስደተኞች ያረፉባቸው የተወሰኑ የአውሮፓ ሀገራት የበለጠ ተጎጂ መሆናቸውን ተከትሎ ውይይቱ ያለ ስምነት ይጠናቀቃል ተብሎ ተፈርቶ ነበርም ተብሏል፡፡
ይሁንና ህብረቱ ባወጣው መግለጫ ወደ አውሮፓ በሚገቡ ስደተኞች ዙሪያ ወጥ ምላሽ ለመስጠት አባል ሀገራቱ መስማማታቸውን አስታውቋል፡፡
በዚህ ስምምነት መሰረትም ወደ አውሮፓ የሚገቡ ስደተኞችን ቁጥር ለመወሰን፣ አቀባበል ለማድረግ እና ጥብቅ የጋራ ቁጥጥር ማድረግ ዋነኞቹ የስምምነቱ አካል ናቸው፡፡
ይህ አዲስ ስምምነት ከጥቂት ቀናት በኋላ ከሚገባው የፈረንጆቹ 2024 ዓመት ጀምሮ ይተገበራል የተባለ ሲሆን በገፍ ወደ አውሮፓ የሚገቡ ስደተኞችን ቁጥር ለመቀነስ ይጠቅማልም ተብሏል፡፡
ትራምፕ ስደተኞች "ደማችንን እየበከሉ ነው" የሚለውን ንግግራቸውን ደገሙት
በአውሮፓ በተያዘው የ2023 ዓመት ውስጥ ብቻ 255 ሺህ ስደተኞች ከተለያዩ ሀገራት ወደ አውሮፓ እንደገቡ ህብረቱ አስታውቋል፡፡
ወደ አውሮፓ ከገቡ ስደተኞች መካከል አብዛኞቹ አፍሪካዊያን ሲሆኑ ጣልያን እና ማልታ ደግሞ ዋነኛ የስደተኞች ማረፊያ ሀገራት ናቸው፡፡
እንደ ጣልያን ያሉ ስደተኛ የበዛባቸው ሀገራት ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ካላገዙ ስደተኞቹን እንደሚለቁ ማሳሰባቸውን ተከትሎ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራቱን በማስተባበር ከዚህ ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ ማድረጉ ተገልጿል፡፡
በአዲሱ የስደተኞች ፖሊሲ ስምምነት መሰረት ጥገኝነት የሚጠይቁ ስደተኞች ጥያቄያቸው ውድቅ የመደረጉ እድል ከፍተኛ ነው የተባለ ሲሆን በተለይም ከቱርክ፣ ቱኒዝያ እና ሕንድ የመጡ ስደተኞች ዋነኛ ተጎጂ ሊሆኑ እንደሚችል ተጠቅሷል፡፡