እስራኤል በጃባሊያ የስደተኞች ካምፕ ባደረሰችው ጥቃት የሀማስን አዛዥ ገደልኩ አለች
የሀማስ ቃል አቀባይ ሀዘም ቃሴም ከፍተኛ የተባለ አዛዥ በካሞፑ ውስጥ አልነበረም ሲል አስተባብሏል
የእስራኤል ጦር እንደገለጸው በጋዛ ውስጥ ትናንት በተደረገው ውጊያ 11 ወታደሮች ተገድለዋል
እስራኤል በተጨናነቀው የጃባሊያ ስደተኞች ካምፕ ላይ በሰነዘረችው ጥቃት የሀማስን አዛዥ መግደሏን አስታወቀች።
በጥቃቱ 50 ስደተኞች እና አደጋ የደረሰባቸውን ለመታደግ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩ የህክምና ባለሙያዎች መገደላቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
የእስራኤል ጦር እንደገለጸው በጋዛ ውስጥ ትናንት በተደረገው ውጊያ 11 ወታደሮች ተገድለዋል።
እስራኤል በጥቅምቱ የሀማስ ጥቃት 300 ወታደሮቿን እና 1100 ንጹሃን ዜጎቿን ካጣችበት ጥቃት ወዲህ ይህ በአንድ ቀን የደረሰ ትልቅ ጉዳት ነው ተብሏል።
የእስራኤል የጦር ሬድዮ እንደዘገበው የተገደሉት አብዛኞቹ ተሽከርካሪያቸው በጸረ-ብረት ለበስ ሚሳይል የተመታባቸው ናቸው።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል(አይዲኤፍ) ባወጣው መግለጫ በጋዛ በሚገኘው ግዙፉ የጃባሊያ የስደተኞች ካምፕ ላይ ባደረሰው የአየር ጥቃት፣ በእስራኤል ላይ ጥቃት በማቀድ እና በመፈጸም ወሳኝ ሚና ነበረው ያለውን ኢብራሂም ቢያሪን መግደሉን አስታውቋል።
የአይዲኤፍ ቃል አቀባይ ሊዩትናንት ኮሎኔል ጆናታን ኮንሪከስ ቢያሪ በነበረበት ቱቦ ውስጥ የነበሩ በደርዘን የሚቆጠሩ የሀማስ ተዋጊዎችም ተገድለዋል ብለዋል።
የሀማስ ቃል አቀባይ ሀዘም ቃሴም ከፍተኛ የተባለ አዛዥ በካሞፑ ውስጥ አልነበረም ሲል አስተባብሏል።
ቃሴም ይህ እስራኤል ንጹሃንን ለማጥቃት ስትፈልግ እንደሰበብ የምትጠቀምበት ነው ብሏል።
የፍልስጤም ባለስልጣናት በካምፑ ላይ ባደረሰችው ጥቃት 50 ሰዎች መገደላቸውን እና 150 የሚሆኑ ደግሞ መቁሰላቸውን ተናግሯል።
ሀማስን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት የወሰነችው እስራኤል በጋዛ ውስጥ የጥቃት ቀጣናዋን በማስፋት ላይ ትገኛለች።