የሃማስ የፖለቲካ መሪው ኢስማኤል ሀኒየህ እህትን ጨምሮ 10 ዘመዶቻቸው ተገደሉ
እስራኤል በአል ሻቲ የስደተኞች ጣቢያ ላይ በፈጸመችው ጥቃት ነው የሀኒየህ ዘመዶች የተገደሉት
ሃኒየህ ሶስት ልጆቻቸው በሚያዚያ ወር ሲገደሉ፥ “መስዋዕትነት በሚከፍሉ ወገኖቻችን ነጻነታችን እናውጃለን” ማለታቸው ይታወሳል
እስራኤል በሰሜናዊ ጋዛ በፈጸመችው የአየር ጥቃት የሃማስ የፖለቲካ መሪው ኢስማኤል ሀኒየህ 10 ዘመዶች መገደላቸው ተገለጸ።
ከሟቾቹ መካከልም የሀኒየህ እህት ዛህር ሃኒየህ እንደሚገኙበት ነው የሃማስ ባለስልጣናትን ጠቅሶ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዘገበው።
በአል ሻቲ የስደተኞች ጣቢያ በሚገኝ የሀኒየህ ቤተሰቦች ቤት ላይ ባነጣጠረው ጥቃት ህይወታቸው ያለፈው 10 ሰዎች በፍርስራሽ ውስጥ እንደሚገኙም ነው የተገለጸው።
የእስራኤል ጦር በበኩሉ በአል ሻቲ እና ዳራጅ ቱፋህ በተባሉት የስደተኞች ጣቢያዎች ላይ ጥቃቱ የተፈጸመው የሃማስ ታጣቂዎች መደበቂያ ስለነበሩ ነው ብሏል።
ጦሩ ስለሟቾቹ ማንነት ግን ከመጥቀስ ተቆጥቧል።
በኳታር መዲና ዶሃ የሚኖሩት የሃማስ የፖለቲካ ቢሮ ሃላፊው ኢስማኤል ሃኒየህ በሚያዚያ ወር ሶስት ልጆቻቸውንና አራት የልጅ ልጆቻቸውን በእስራኤል የአየር ጥቃት ማጣታቸው ይታወሳል።
ሃኒየህ በወቅቱ እስራኤል በጋዛ ድብደባ ከጀመረች አንስቶ ከ60 በላይ ቤተሰቦቻቸው መገደላቸውን መናገራቸውም አይዘነጋም።
“የልጆቼ ደም ከህዝባችን የተለየ አይደለም፤ እስራኤል ልጆቼን በመግደል ሃማስ አቋሙን ይለውጣል የሚል የቅዠት ሀሳብ አስባ ይሆናል ግን ይሄ በፍጹም አይሆንም” ያሉት ሃኒየህ፥ “መስዋዕትነት በሚከፍሉና በሚቆስሉ ወገኖቻችን ነጻነታችን እናውጃለን” የሚል አስተያየት ሰጥተው ነበር።
ሃማስ እና መሪዎቹን በሽብርተኝነት የፈረጀችው እስራኤል የፍልስጤሙ ቡድን ሙሉ በሙሉ ካልተደመሰሰ በቀጣይም እንደ ጥቅምት 7ቱ አይነት ጥቃት ያደርስብኛል የሚል ስጋት አላት።
ይህም ከ37 ሺህ 600 በላይ ፍልስጤማውያንን ህይወት የቀጠፈውን ጦርነት በዘላቂነት ለማስቆም የሚደረጉ ድርድሮች ላይ ተጽዕኖ ማሳረፉ ይነገራል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከሰሞኑ ታጋቾችን የሚያስለቅቅ እና ሰብአዊ ድጋፍን ለማስገባት የሚያግዝ “ከፊል የተኩስ አቁም ስምምነት” እንጂ ከጋዛ የሚያስወጣን ስምምነት አንፈርርም ማለታቸው ይታወሳል።
ሃማስ የጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ አስተያየት ጦርነቱ እንዲቆም እንደማይፈልጉ ማሳያ አድርጎ ያቀረበው ሲሆን፥ የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝም በጋዛ አስቸኳይ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ አሳስበዋል።
የእስራኤል እና ሊባኖስ ድንበር ውጥረት እያየለ መሄድም ተመድን እንደሚያሳስበው ነው የተናገሩት።
የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር ዮቭ ጋላንት ቴል አቪቭ ከቤሩት ጋር ጦርነት ብትጀምር ድጋፍ እንደምትሰጣት ወዳረገገጠችው አሜሪካ በማቅናት ምክክር እያደረጉ ነው።
የዋሽንግተን ድጋፍ ስምንት ወራት ያለፈው የጋዛ ጦርነት አድማሱን እያሰፋ እንዲሄድ ሊያደርገው ይችላል የሚለው ስጋትም ጨምሯል።