የእንስሳት አማካይ የእድሜ ጣራ (በዓመት)
የሰው ልጅ 100 ዓመታትን ለተሻገረ ጊዜ በምድር ላይ ሲቆይ አጃኢብ በያስብልም 15 ሺ አመታትን የሚኖር የባሕር እንስሳ እንዳለ ብንነግረዎ ምን ይላሉ?

ከ24 ሰአታት ያነሰ እድሜ ጀምሮ እስከ ሺህ አመታት ድረስ የሚኖሩ የተለያየ ዝርያ ያላቸው እንስሳቶችን ተፈጥሮ ታቅፋለች
ሰዎች በምድር ላይ የሚኖራቸው ረጅም እድሜ ቆይታ እስከ 150 ዓመት ድረስ ቢለጠጥ እንኳን አንዳንድ እንስሳት ከሚኖሩባቸው ክፍለ ዘመናት እና ሺህ ዓመታት ጋር ሲነፃፀር የዓይን ጨረፍታን ያህል የሚቆጠር ነው።
ትክክለኛዎቹ የከፍተኛ እድሜ ባለጸጎች መኖርያቸው በጥልቁ ውሀ ውስጥ ነው፤ የሳይንስ ሊቃውንት የእያንዳንዱን የእንስሳት ዝርያ ውልደት እና ሞት መመዝገብ ባይችሉም ካላቸው ልዩ ስነ ህይወታዊ ፍጠረት እና ከአኗኗራቸው በመነሳት የእድሜ ጣራቸውን በምርምር ያስቀምጣሉ፡፡
አንዳንድ የዔሊ ዝርያዎች ፣ ሻርኮች እና አሳ ነባሪዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ አመታትን እንደሚኖሩ ቢታወቅም፤ በአንታርክቲካ የባሕር ክፍል መኖርያውን ያደረገው “ሲ ስፖንጅ” የተባለው የባህር ፍጡር ለ15 ሺህ አመታት በመኖር ተወዳዳሪ አልተገኝለትም፡፡
አንዳንድ እንስሳት “ባዮሎጂካል ኢሞርታሊቲ” የሚባል ብርቅዬ ባህሪ አላቸው፣ እነዚህ ፍጡራን ሴሎቻቸው ወሰን በሌለው ሁኔታ እንደገና እንዲፈጠሩ እና እንዲያድጉ በማድረግ ተፈጥሯዊ እርጅናን ይከላከላሉ።
“ባዮሎጂካል ኢሞርታል” በሚል ከሚጠሩ የባህር እንስሳት መካከል ሲ ስፖንጅ ፣ ጄሊፊሽ እና ሎብስተር ይጠቀሳሉ
ይሁን እንጂ እነዚህ እንስሳት የማይሞቱ ተብለው ቢጠቀሱም ለዘለአለም መኖር አይችሉም ከጊዜ ብዛት የሴል እድገት መዳከመ ፣ በበሽታ እና በአካባቢያዊ ለውጦች ሊሸነፉ ይችላሉ፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን ለ24 ሰአታት እና ከዛ በታች ከሚኖረው “ሜይ ፍላይ” በተለምዶ “የእሳት እራት” በመባል ከሚታወቀው በራሪ እንስሳ ጀምሮ በምድር ላይ የሚገኙ እንስሳት እስከ ሺህ አመታት ድረስ በህይወት ይኖራሉ፡፡
ላይቭ ሳይንስ የተባለው ከእንስሳት ጋር በተገናኝ የተለያዩ የምርምር ስራዎችን የሚያወጣው ድረ ገጽ ይፋ ባደረገው መረጃ አይጦች በአማካይ አንድ አመት እንደሚኖሩ አመላክቷል፡፡
ካንጋሮ ፣ ዶሮ እና ውሻ ዝቅተኛ የሚባል የእድሜ ጣርያ ካላቸው እንስሳት መካከል ይጠቀሳሉ፤በአንጻሩ ዔሌዎች በእንስሳት የ100 ዓመት እድሜ መጀመርያ ተደርገው ይቆጠራሉ፡፡
በተለይም መገኛውን በሲሼልስ ደሴቶች ያደረገው 250 ኪሎግራም የሚመዝነው “አልዳብራ” በሚል ስያሜ የሚጠራው ኤሊ ከ150 አመት በላይ ይኖራል፡፡
በጨዋማ ውሀዎች የሚኖሩ አዛዎች በበኩላቸው የጎልማሳነት እድሜን ካለፉ 120 እና ከዛ በላይ አመታትን ይሻገራሉ፡፡
አሳ ነባሪ እና የግሪንላንድ ሻርክ በሚል መጠርያ የሚታወቁት የአሳ ዝርያዎች ደግሞ ከ200 እስከ ግማሽ ሚሊኒየም እድሜን በመኖር ተጠቃሽ ናቸው፡፡