ትራምፕ ህገወጥ ስደተኞች “እንስሳት” ናቸው አሉ
አወዛጋቢው ሰው በቀጣዩ ምርጫ ካልተመረጥኩ አሜሪካ በህገወጥ ስደተኞች ሁከትና ግድያ ትታመሳለች፤ የሀገሪቱም የመጨረሻው ምርጫ ይሆናል ብለዋል
ጥናቶች ግን ህገወጥ ስደተኞች ከአሜሪካ ተወላጆች በበለጠ አሰቃቂ ወንጀሎችን እንደማይፈጽሙ ያሳያሉ
የአሜሪካ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሚቺጋን ባደረጉት የምርጭ ቅስቀሳ ህገወጥ ስደተኞችን ከሰዎች መቁጠር እንደሚቸገሩ ተናግረዋል።
በህገወጥ ስደተኞች እየተፈጸሙ ያሉ አሰቃቂ ወንጀሎች መበራከታቸውን በመጥቀስም ድርጊቱን እየፈጸሙ ያሉ ስደተኞች “እንሰሳት” ናቸው ሲሉም ነው የገለጹት።
አወዛጋቢው ሰው እነዚህን አሜሪካን አዘቅት ውስጥ እየከተቱ ያሉ አካላት አደብ ለማስገዛት ልትመርጡኝ ይገባል፤ ካልሆነ ግን በሀገሪቱ ሁከትና አሰቃቂ ግድያው ይቀጥላል ማለታቸውንም ሬውተርስ ዘግቧል።
ስደተኞችን በመርዛማ ቃላት በመግለጽ የሚታወቁት ትራምፕ የሜክሲኮን ድንበር አቋርጠው በህገወጥ መንገድ አሜሪካ የሚገቡ ሰዎች ከእስርቤቶች ያመለጡ ናቸው ብለዋል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት በህገወጥ ስደተኞች እየተፈጸሙ ያሉ ወንጀሎች መበራከትንም ሆነ ከላቲን አሜሪካ እስር ቤቶች ወደ አሜሪካ እንዲገቡ እየተደረገ ነው ለሚለው ክሳቸው የሚጨበጥ አሃዛዊ ማስረጃ ግን አላቀረቡም።
ትራምፕ ህገወጥ ስደተኞች “ድማችን እየበከሉ ነው”፤ አሰቃቂ ወንጀሎችንም እያስፋፉ ነው የሚሉ ወቀሳዎችን በየምርጫ ቅስቀሳቸው ቢያነሱት ህገወጥ ስደተኞች ከአሜሪካ ተወላጆች በበለጠ አሰቃቂ ወንጀሎችን እንደማይፈጽሙ ነው ጥናቶች ያሳዩት።
የሪፐብሊካኑ እጩ ተፎካካሪ ስደተኛ ጠል አቋማቸውን ደጋግመው እያሰሙ ቢሆንም ኮንግረንሱ በደቡባዊ የሀገሪቱ ክፍል ህገወጥ ስደትን ለመከላከል የሚውል ህግ እንዳያጸድቅ ግፊት ሲያደርጉ ነበር ተብሏል።
ዴሞክራቱ ተፎካካሪያቸው ጆ ባይደንም ይህን የትራምፕ እንቅስቃሴ የተቃወሙ ሲሆን፥ የትናንቱ ንግግራቸውም ጥላቻና መከፋፈልን ያሰፋል በሚል ትችት ገጥሞታል።
ትራምፕ በዊስኮንሲን ባደረጉት ንግግርም በአሜሪካ ከተሞች የሚፈጸሙ ግድያና አስገድዶ መድፈር ወንጀሎችን ለማስቆም ቃል የገቡ ሲሆንል በህዳር ወሩ ምርጫ ካላሸነፍኩ “የአሜሪካ የመጨረሻ ምርጫ” ይሆናል ማለታቸው አነጋጋሪ ሆኗል።