እስራኤል የኢራንን ሚሳኤል ለማክሸፍ ከ450 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ማድረጓ ተገለጸ
ኢራን እስራኤልን ለመምታት የተኮሰቻቸው ሚሳኤሎች ምን ህል ዋጋ ያወጣሉ?
ሚሳኤል ከመተኮስ ይልቅ ማክሸፍ የበለጠ ውድ መሆኑን ባለሙያዎች ይገልጻሉ
እስራኤል የኢራንን ሚሳኤል ለማክሸፍ ከ450 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ማድረጓ ተገለጸ፡፡
ለፍልስጤም ነጻነት የሚታገለው ሐማስ በእራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ በመካከለኛው ምስራቅ የተጀመረው ጦርነት አንድ ዓመት ሊሞላው ሁለት ቀናት ብቻ ቀርቶታል፡፡
ሐማስ እና የሊባኖሱ ሂዝቦላህ በኢራን ይደገፋሉ ብላ የምትጠረጥረው እስራኤል የቡድን መሪዎችን የገደለች ሲሆን ይህም ኢራንን አስቆጥቷል፡፡
እስራኤል ላደረገችው ጥቃት ኢራን ከሰሞኑ በእስራኤል ላይ የሚሳኤል ጥቃት አድርሳለች። 200 ሚሳኤሎችን ወደ እስራኤል ከተሞች የተኮሰችው ኢራን 200 ሚሊዮን ዶላር ወጪ አድርጋለች ተብሏል፡፡
በአንጻሩ እስራኤል ከኢራን የተተኮሱባትን ሚሳኤሎች ለማክሸፍ ከ450 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ እንዳደረገች ጀረሰላም ፖስት ዘግቧል፡፡
እንደ ዘገባው ከሆነ አንድ ሚሳኤልን ለማምረት አንድ ሚሊዮን ዶላር ወጪ የሚጠይቅ ሲሆን ሚሳኤልን ከማምረት ይልቅ ማክሸፍ የበለጠ ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል፡፡
እንደ እስራኤል መከላከያ ሪፖርት ከሆነ ኢራን ከአምስት ቀናት በፊት 181 ሚሳኤሎችን ወደ እስራኤል የተኮሰች ሲሆን አሜሪካ እና እስራኤል በጋራ በመሆን ሚሳኤሎቹን ለማክሸፍ ሞክረዋል፡፡
በኢራን ከተተኮሱት ሚሳኤሎች ውስጥ 12ቱ በመካከለኛው ምስራቅ ያለው የአሜሪካ ጦር መክሸፋቸው ተገልጿል፡፡
ኢራን እስከ 2 ሺህ ኪሎ ሜትር ያሉ ኢላማዎችን መምታት የሚችሉት ኢማድ፣ ካይባር እና ፋቴህ የተሰኙ ሚሳኤሎችን ወደ እስራኤል ከተኮሰቻቸው ሚሳኤሎች መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡
እስራኤል ሚሳኤሎችን እና ሌሎች የአየር ላይ ጥቀቶችን ለማክሸፍ የምትጠቀምበት አይረን ዶም የሚባለው መሳሪያ አብዛኞቹን የኢራን ሚሳኤሎችን አክሽፏል ተብሏል፡፡
የእስራኤል ካቢኔ በትናንትናው ዕለት በኢራን ላይ የአጸፋ እርምጃ እንዲወሰድ ውሳኔ አሳልፏል።
ኢራን በበኩሏ እስራኤል የአጸፋ ጥቃት ከሰነዘረች ከባድ ጥቃት ይጠብቃታል ስትል አስጠንቅቃለች።