እስራኤል የኢራንን ኑክሌር ማብለያ ጣቢያን መምታት አለባት ብለው እንደሚያምኑ ዶናልድ ትራምፕ ተናገሩ
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከሰሞኑ ከዶናልድ ትራምፕ ተቃራኒ ሀሳብ መስጠታቸው ይታወሳል
የእስራኤል ካቢኔ በኢራን ላይ የአጸፋ እርምጃ እንዲወሰድ ውሳኔ አሳልፏል
እስራኤል የኢራንን ኑክሌር ማብለያ ጣቢያን መምታት አለባት ብለው እንደሚያምኑ ዶናልድ ትራምፕ ተናገሩ።
አንድ ዓመት ሊሆነው ሁለት ቀናት ብቻ የቀሩት የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት አሁንም የቀጠለ ሲሆን ኢራን እና እስራኤል ወደ መደበኛ ጦርነት እንዳይገቡ ተሰግቷል፡፡
እስራኤል በኢራን ይደገፋሉ የሚባሉት የሊባኖሱ ሂዝቦላህ እና የፍልስጤሙ ሐማስ መሪዎችን እየገደለች ትገኛለች።
እስራኤል ላደረገችው ጥቃት ኢራን ከሰሞኑ በእስራኤል ላይ የሚሳኤል ጥቃት አድርሳለች።
ይህን ተከትሎ እስራኤል በኢራን ላይ የአጸፋ እርምጃ እንደምትወስድ የዛተች ሲሆን ብዙዎች መካከለኛው ምስራቅ ወደ ተባባሰ ጦርነት እንዳይገባ ሰግተዋል።
የእስራኤል ዋነኛ አጋር የሆነችው አሜሪካ ከአንድ ወር በኋላ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ታካሂዳለች።
በዚህ ምርጫ ላይ ዋነኛ እጩ የሆኑት ዶናልድ ትራምፕ እስራኤል የኢራን ኑክሌር ማብለያ ጣቢያን መምታት አለባት ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት እስራኤል የኢራንን ኑክሌር ጣቢያ መምታት አለባት ብለው ያምናሉ? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ አዎ መምታት አለባት ብዬ አምናለሁ ብለዋል።
ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከሰሞኑ ተመሳሳይ ጥያቄ ቀርቦላቸው ኢራን እስራኤልን ማጥቃቷ ስህተት ነው ነገር ግን እስራኤል የቴህራንን ኑክሌር ጣቢያ መምታት አለባት ብዬ አላምንም ሲሉ ተናግረው ነበር።
ፕሬዝዳንት ባይደን የኢራን ነዳጅ ማውጫ ጣቢያዎች የእስራኤል አጸፋ ጥቃት ኢላማ ሊሆኑ እንደሚችሉ የተናገሩ ሲሆን ኢራን በበኩሏ እስራኤል የአጸፋ ጥቃት ከሰነዘረች ከባድ ጥቃት ይጠብቃታል ስትል አስጠንቅቃለች።
የእስራኤል ካቢኔ በትናንትናው ዕለት በኢራን ላይ የአጸፋ እርምጃ እንዲወሰድ ውሳኔ አሳልፏል።