የአለም ዋንጫው አሸናፊና ተሳታፊዎቹ ምን ያህል ገንዘብ ይሸለማሉ?
ኳታር ባስተናገደችው 22ኛው የአለም ዋንጫ አሸናፊ የምትሆነው ሀገር 42 ሚሊየን ዶላር ታገኛለች
በዚህ አመት ለግማሽ ፍፃሜ የደረሱት ሀገራት ከ2006ቱ የአለም ዋንጫ ሻምፒዮን የተሻለ ሽልማት ያገኛሉ
የ22ኛው የአለም ዋንጫ ሻምፒዮን 42 ሚሊየን ዶላር ይዞ ወደ ሀገሩ ይመለሳል።
ይህም ሩስያ ካስተናገደችው የ2018ቱ የአለም ዋንጫ የ4 ሚሊየን ዶላር ብልጫ ያለው ነው።
ባለፉት አራት አስርት አመታት በአለም ዋንጫው አሸናፊ ለሚሆኑና ለተሳታፊዎቹ እንደየደረጃቸው የሚበረከትላቸው ሽልማት እያደገ መጥቷል።
የአለም ዋንጫው ሻምፒዮና ከ10 ሚሊየን ዶላር በላይ መሸለም የጀመረው በ2006 ነው፤ ጣሊያን ዋንጫውን አንስታ 20 ሚሊየን ዶላርን ወደ ሮም ይዛ ተመልሳለች። አዙሪዎቹ በ1982 ዋንጫ ሲያነሱ የወሰዱት ሽልማት ግን 2 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር ነው።
በመካከለኛው ምስራቅ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተካሄደ ባለው የኳታሩ የአለም ዋንጫ የሽልማቱ ገንዘብ አድጓል።
ሻምፒዮን የምትሆነው ሀገርና ሌሎች ተፋላሚዎች የሚያገኙት ሽልማት እንደሚከተለው ቀርቧል፦
ዋንጫውን ለሚያነሳ ሀገር - 42 ሚሊየን ዶላር
የፍፃሜው ተፋላማ ሀገር - 30 ሚሊየን ዶላር
ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀ - 27 ሚሊየን ዶላር
አራተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀ - 25 ሚሊየን ዶላር
ሩብ ፍፃሜ የደረሱ - 17 ሚሊየን ዶላር
16 ውስጥ የገቡ - 13 ሚሊየን ዶላር
የምድብ ጨዋታዎችን ያደረጉ - 9 ሚሊየን ዶላር ያገኛሉ።
ፊፋ ባወጣው የሽልማት መጠን መረጃ መሰረት በዚህ አመት ግማሽ ፍፃሜ የደረሱት ሀገራት ከ2006ቱ የአለም ዋንጫ ሻምፒዮን የተሻለ ሽልማት ያገኛሉ።
በአለም ዋንጫው የተሳተፉ ተጫዋቾችም የሽልማቱ ተቋዳሽ ናቸው ተብሏል።