“አውሮፓውያን በስደተኞች አያያዝ ኳታርን የመክሰስ ሞራል የላቸውም” - ኢንፋንቲኖ
የፊፋ ፕሬዚዳንት ጂያኒ ንፋንቲኖ ኳታር የአለማችን ምርጡን የአለም ዋንጫ አዘጋጅታለች ብለዋል
ከሰብአዊ መብት እና ከስደተኞች አያያዝ ጋር በተገናኘ በኳታር ላይ የተከፈተውን ዘመቻም አጣጥለዋል
የፊፋ ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ አውሮፓውያን በኳታር ላይ ጣታቸውን ለመቀሰር ሞራል የላቸውም አሉ።
ኢንፋንቲኖ በዶሃ በሰጡት መግለጫ ኳታር የአለማችን ምርጡን የአለም ዋንጫ አዘጋጅታለች ብለዋል።
ኳታር 22ኛውን የአለም ዋንጫ እንደምታዘጋጅ ከተገለፀ ጀምሮ ከሰብአዊ መብት እና ከስደተኞች አያያዝ ጋር በተገናኘ የተለያዩ ክሶች ሲቀርቡባት ከርመዋል።
ዶሃ በመካከለኛው ምስራቅ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደው የአለም ዋንጫ እንዲሰረዝ የቀድሞው የፊፋ ፕሬዚዳንት ሴፕ ብላተርን ጨምሮ በርካቶች ግፊት ሲያደርጉ እንደነበር ይታወሳል።
ኢንፋንቲኖ ግን ከዚህ የተቃረነ አስተያየታቸውን በመግለጫቸው አንስተዋል።
"እኛ አውሮፓውያን ባለፉት 3 ሺህ አመታት ላጠፋነው ለቀጣይ 3 ሺ አመት ይቅርታን ሳንጠይቅ ለሌሎች ስለሞራል ማስተማር አንችልም" ሲሉ ነው የተደመጡት።
ኳታርን የመውቀስ የሞራል ልዕልና የለንም ያሉት ኢንፋንቲኖ፥ ዶሃ ምርጡን የአለም ዋንጫ ለማስተናገድ ዝግጁ ሆናለችም ብለዋል።
ከጣሊያናዊያን ቤተሰብ የተወለዱት ኢንፋንቲኖ በስራ ምክንያት ከወላጆቻቸው ጋር ወደ ስዊዘርላንድ ባቀኑበት ወቅት የገጠማቸውን መገለልና መድልኦ ከዚህ ቀደም አንስተዋል።
በዛሬው መግለጫቸውም ከአጠቃላይ ህዝቧ 85 ከመቶው የሌላ ሀገር ዜጋ የሚኖርባት ኳታር ላይ ጣት የሚቀስሩ አካላትን ቆም ብላችሁ አስቡ ብለዋቸዋል።
አውሮፓውያን ሀገራት አሁን ላይ ለስደተኞች ድንበራቸውን መዝጋታቸውን አንስተው ኳታር በአንፃሩ ለህንድ፣ ባንግላዲሽ እና ደቡብምስራቅ እስያ ሀገራት ለሚመጡ ሰራተኞች በሯን ከፍታ እንደምትጠብቅ አብራርዋል።
ስምንቱን የኳታር ስታዲየሞች በመገንባቱ ሂደት ህይወታቸው ያለፈ ስደተኞች መኖራቸውንና የሚከፈላቸውም ዝቅተኛ ገንዘብ ነው የሚሉ ምዕራባውያን በኳታር ላይ ዘርፈ ብዙ ጫና ሲያሳድሩ ቆይተዋል።
ኢንፋንቲኖ ግን ለምዕራባውያኑ መገናኛ ብዙሃን ጩኸት ቁብ ሳይሰጡ "ባለፉት ወራት አስደማሚ ስራዎች ተከናውነዋል" ብለዋል።