የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ የደረሱት እስራኤል እና ሄዝቦላ የተኩስ ልውውጥ እያደረጉ ናቸው ተባለ
እስራኤል ይህን ጥቃት የፈጸመችው ሄዝቦላ የተኩስ አቁም ስምምነት ጥሳለች የሚል ክስ ካቀረበባት ከጥቂት ቆይታ በኋላ ነው
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ቃል አቀባይ ስምምነቱ ተጥሷል የሚሉ ሪፖርቶችን ለመመርመር ከፈረንሳይ፣ እስራኤል እና ሊባኖስ ጋር እየተናገሩ መሆናቸዉን ተናግረዋል
የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ የደረሱት እስራኤል እና ሄዝቦላ የተኩስ ልውውጥ እያደረጉ ናቸው ተባለ።
እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ በሚገኙ ታሎሳ እና ሀሪስ በተባሉ ሁለት ከተሞች ላይ በፈጸመችው የአየር ጥቃት ቢያንስ ዘጠኝ ሰዎች መገደላቸውን እና ሌሎች ሶስት መቁሰላቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
የሊባኖስ ባለስልጣናት ሰኞ እልት ጠዋት በሌላ የሊባኖስ ክፍል በስራ ላይ የነበረን የሀገሪቱን የደህነት አባል ጨምሮ ሁለት ሰዎች በእስራኤል የአየር ጥቃት መገደላቸውን ሪፖርት ያደረጉ ሲሆን ይህም በእለቱ የተገደሉ ሰዎችን ቁጥር ወደ 11 ከፍ ያደርገዋል።
እስራኤል ይህን ጥቃት የፈጸመችው ሄዝቦላ የተኩስ አቁም ስምምነት ጥሳለች የሚል ክስ ካቀረበባት ከጥቂት ቆይታ በኋላ ነው።
ምሽቱን ድሮኖች ዝቅ ብለው ሲበሩ እንደነበር ሮይተርስ ነዋሪዎችን ጠቅሶ ዘግቧል።
የተኩስ ልውውጡ በአሜሪካ አደራዳሪነት ከተደረሰ አንድ ሳምንት የሆነውን የተኩስ አቁም ስምምነት በአደጋ ውስጥ የሚጥል ነው። ስምምነቱ እስራኤል የማጥቃት ዘመቻ እንዳታደርግ የሚከለከል ሲሆን ሊባኖስ ደግሞ ታጣቂ ቡድኑ ወደ ሊባኖስ ጥቃት እዳይፈጽም የማድረግ ግዴታ ጥሎባታል።
የእስራኤል ጦር ሄዝቦላ ያስወነጨፋቸው ሚሳይሎች ጉዳት አለማድረሳቸውን ሪፖርት አድርጓል፤ ነገርግን ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ "ጠንካራ" ምላሽ እንሰጣለን ሲሉ ዝተዋል።
የተኩስ አቁም ስምሞነቱ ባለፈው ረቡዕ ከተደረሰ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሮኬት ወደ እስራኤል ያስወነጨፈው እስራኤል ላደረሰችው ተደጋጋሚ ጥስት ምላሽ ነው ብሏል።
ሊባኖስን ወክሎ በተኩስ አቁም ድርድሩ የተሳተፈው የሊባኖስ አፈጉባኤ ቤይሩት ከባለፈው ረቡዕ ጀምሮ እስራኤል ለ54ኛ ጋዜ ስምምነቱን መጣሷን መዝግባለች ብለዋል።
የሊባኖስ ዜና አገልግሎት ኤንኤንኤ የእስራኤል ኃይሎች በደቡብ ሊባኖስ ቢንት ጀቢል አስተዳደር ውስጥ ወደምትገኘው ቤይት ሊፍ ከተማ ሁለት ጊዜ በከባድ መሳሪያ መተኮሳቸውን ዘግቧል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማቲው ሚለር ስምምነቱ ተጥሷል የሚሉ ሪፖርቶችን ለመመርመር ከፈረንሳይ፣ እስራኤል እና ሊባኖስ ጋር እየተናገሩ መሆናቸዉን ተናግረዋል።