ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት አጣሪ ኮሚሽን ያወጣውን ሪፖርት ውድቅ አደረገች
አጣሪ ኮሚሽኑ “ረሃብ፣ ወሲዊ ጥቃትና ሌሎች የመብት ጥሰቶች እንደ ጦር መሳሪያነት ጥቅም ላይ ውለዋል” ብሏል
ኢትዮጵያ የተመድ ሪፖርት “ፖለቲካዊ ውግንና ያለው፣ እርስ በእርሱ የሚጣረስና ወገንተኛ ነው” ብላለች
ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት አጣሪ ኮሚሽን የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት በማስመልከት ያወጣውን ሪፖርት ውድቅ አደረገች።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን የኤክስፐርቶች ቡድን ከ2 ዓመት በፊት በትግራይ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ በሁሉም ወገኖች የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን የሚያሳይ ማስረጃ ማግኘቱን ትናንት ባወጣው ሪፖርቱ አስታውቋል።
“በኢትዮጵያ ሰራዊት በትግራይ ክልል በነበረባቸው ጊዜያቶች ላማዊ ዜጎች ላይ ግድያዎች መፈጸሙን መረጃ አግኝቻለው” ያለው ሪፖርቱ፤ “የህወሓት ኃይሎች በአማራ ክልል በቆዩባቸው ጊዜያቶችም ግድያዎች፣ ድብደባዎች፣ መደፈርና የአማራን ብሔር የሚያንቋሽሹ ስድብ ይሳደቡ ነበር” ብሏል።
በተጨማሪም መርማሪዎች “ረሃብን አና መድሃኒቶችን መከልከል እንደ ጦር መሳሪያነት ጥቅም ላይ እየዋለ ስለመሆኑ የሚያሳዩ መረጃዎችም አሉ” ብለዋል።
ይህንን ሪፖርት ተከትሎ በጄኔቭ የተባሩት መንግሰትታት የኢትዮጵያ ቋሚ መልእክተኛ አምባሳደር ዘንበ ከበደ፤ የተመድ የሰብአዊ መብት አጣሪ ኮሚሽን ያወጣውን ሪፖርት ፖለቲካዊ አላማን የያዘ ነው ሲሉ አጣጥለውታል።
የሰብአዊ መብት አጣሪ ኮሚሽን ያወጣው ሪፖርት ድምዳሜዎች እርስ በእርሱ የሚጣረስ እና ወገንተኛ መሆኑን ለኤ.ኤፍ.ፒ ተናግረዋል።
"የኢትዮጵያ መንግስት ሰብአዊ እርዳታን እንደ ጦር መሳሪያ መጠቀሙን የሚያሳይ አንድም ማስረጃ በሪፖሩቱ አልቀረብም" ያሉት መልዕክተኛው ሪፖርቱን "ፌዝ" እና "የማይረባ" ነው ሲሉ ገልጸውታል።
"ስለዚህ ይህንን ሪፖርት ውድቅ ከማድረግ ውጭ ሌላ አማራጭ የለንም" ሲሉም ቋሚ መልእከተኛው ተናግረዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬደዋን ሁሴን በበኩላቸው በትዊተር ገጻቸው ባጋሩት ጹሁፍ “ሪፖርቱ ኢትዮጵያን ዝቅ የማድረግ ፖለቲካዊ ስራ ውጤት ነው” ሲሉ አጣጥለዋል
ሪፖርቱ ኢትዮጵያን የመወንጀል አላማ እንዳለው የገለጹት አምባሳድር ሬድዋን፤ ሪፖርቱ እስር በእርሱ የሚጣረስ እና ተዓማኒነት የሌለው ነው ሲሉ ገልጸውታል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ቢሮ በትግራይ ግጭት ዙሪያ ያደረጉትን የጋራ ምርመራ ሪፖርት ከወራ በፊት ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል አድርገዋል።
በሪፖርታቸውም በግጭቱ ተሳታፊ አካላት መጠኑ ቢለያይም የሰብአዊ መብት እና ዓለም አቀፍ የስደተኞች መብት ጥሰቶችን ጨምሮ እስከ ጦር ወንጀል ሊደርሱ የሚችሉ ጥሰቶችን መፈፀማቸውን አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ቢሮ ምርመራ እያለ ሌላ ምርመራ አያስፈልግም በሚል ተቃውሞ አቅርባ እንደነበረ ይታወሳል።