የሲቪክ ማህበራት አመራሮች ከመንግስት አካላት በሚደርስባቸው ጫና ከሀገር መሰደዳቸው ተነገረ
ሶስት የሲቪል ማህበራት ድርጅቶችም ያለቅድመ ማስጠንቀቂያ መታገዳቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል አስታውቋል
ማዕከሉ ባወጣው መግለጫ በሲቪል ማህበረሰብ አባላት ላይ ወከባና ማስፈራሪያዎች እየጨመሩ ነው ብሏል
የሲቪል ማህበረሰብ ባለስልጣን ሶስት የሲቪል ማህበራት ድርጅቶችን ማገዱ ተነገረ።
የታገዱት ድርጅቶች የመብቶችና ዴሞክራሲ እድገት ማዕከል(CARD)፣ ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ (AHRE) እና የሕግ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብቶች (LHR) ናቸው ብሏል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ባወጣው መግለጫ።
ማዕከሉ በመግለጫው የሲቪክ ምህዳሩን ሊያጠቡና አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ምልከቶች መኖራቸውን በመጥቀስ መንግስት አፋጣኝ እልባት እንዲሰጣቸው ጠይቋል።
ከተለያዩ የሲቪል ማህበራት አባላትና የመብት ተሟጋች በርካታ አቤቱታዎችን ሲቀበል መቆየቱን ያነሳው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል፥ የተወሰኑ የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች አመራሮች በጽጥታ አካላት በአካልና በስልክ ተደጋጋሚ ወከባና ማስፈራሪያ እንደደረሰባቸው አመላክቷል።
የመብቶች እና ዴሞክራሲ እድገት ማዕከል (CARD) መስራች አቶ አጥናፍ ብርሃኔ እና የኢሰመጉ ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ዳን ይርጋን ጨምሮ የተለያዩ ድርጅቶች መሪዎች በደረሰባቸው ወከባና ማስፈራሪያ ከሀገር ለቀው ለመሰደድ መገደዳቸውንም ነው መግለጫው የጠቆመው።
"ሌሎች የኢሰመጉ ሰራተኞች በሚደርስባቸው ተመሳሳይ ዛቻና ማስፈራሪያ የተነሳ ስራቸውን ተረጋግተው እንዳይሰሩና ለመልቀቅም የተገደዱ መሆኑን ባደረግነው ከትትልና ምርመራ ለመረዳት ችለናል" ይላል መግለጫው።
በሲቪል ማህበረሰቡ ላይ የሚደርሰው ወከባና ማስፈራሪያ ይቀረፋል የሚል ተስፋ ቢኖረንም ምንም አይነት መሻሻል ሳይታይበት ቀጥሏል ያለው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል፥ በሶስት ድርጅቶች ላይ የተላለፈው የእግድ ውሳኔም ተገቢ አይደለም ብሏል።
የሲቪል ማህበረሰብ ባለሥልጣን ድርጅቶቹን ያለበቂ ማስጠንቀቂያ ማገዱ "በቀሩት የሲቪል ማህበረሰቡ አባላት ዘንድ ፍራቻን የሚፈጥርና በሰብአዊ መብቶች ዙሪያ የሚያደርጓቸውን የነቃ ተሳትፎዎችም እጅግ የሚያኮስስ" መሆኑን ነው የጠቆመው።
ከዚህም ባሻገር የመንግስትን ሰብዓዊ መብቶችን የማከበርና የማስጠበቅ ግዴታን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ እና ለሲቪክ ምህዳሩ መጥበብ የጎላ ተጽእኖ የሚያሳድር መሆኑን አብራርቷል።
ድርጅቶቹ ከእገዳው በፊት የተሰጣቸው ምንም አይነት ማስጠንቀቂያም ሆነ የሚያውቁት በግልጽ የተካሄደ ምርመራ አለመኖሩ አካሄዱን ህግን ያልተከተለ፣ ግልጽነት የጎደለው እና በድርጅቶቹ አመራሮችና ሠራተኞች ላይ ድንጋጤን የፈጠረ ድንገተኛ ክስተት አድርጎታል ሲልም አክሏል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል፥ የሲቪል ማህበረሰብ ባለስልጣን መስሪያ ቤት በስሩ የተመዘገቡ ማህበራት ላይ የሚወስደው እርምጃ ግልጽ እና ህግን የተከተለ እንዲሆን ጠይቋል።
ባለስልጣኑ በሲቪል ማህበረሰቡ አባላት ላይ የሚደርሱ ጫናዎችን፣ ወከባዎች፣ ማስፈራሪያዎችንና የመበት ጥሰቶች በመከላከል ረገድ ሃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባም ነው ጥሪ ያቀረበው።