በሰሜን ኮሪያ ራሳቸውን የሚያጠፉ ዜጎች ቁጥር መጨመሩ ተነገረ
ድህነት እና ረሀብ ደግሞ ራስን ለማጥፋት ዋነኞቹ ገፊ ምክንያቶች እንደሆኑ ተገልጿል
በሰሜን ኮሪያ ራስን የማጥፋት ወንጀል በ40 በመቶ ጨምሯል ተብሏል
ከምዕራባዊያን ጋር አተካራ ውስጥ ባለችው ሰሜን ኮሪያ ራሳቸውን የሚያጠፉ ዜጎች ቁጥር መጨመሩ ተገልጿል፡፡
የኮሪያ ደህንነት ሪፖርት እንደሚያሳየው በሰሜን ኮሪያ ራሳቸውን የሚያጠፉ ዜጎች ቁጥር መጨመሩ የፕሬዝዳንት ኪም ጆንግ ኡን መንግስትን አሳስቧል፡፡
የሀገሪቱ መንግስትም ዜጎች ራሳቸውን እንዳያጠፉ የሚከላከል ጊዜያዊ እቅድ ማውጣቱ የተገለጸ ሲሆን እቅዱ ውጤታማ ላይሆን እንደሚችል ተገልጿል፡፡
ሰሜን ኮሪያ በመንግስታቱ ድርጅት እና በአሜሪካ በተጣሉባት የተለያዩ ማዕቀቦች ከዓለም መገለል ያጋጠማት ሲሆን ኢኮኖሚዋም ክፉኛ መጎዳቱን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ማዕቀቦቹን ተከትሎም ዜጎች ለአስከፊ ድህነት እና ረሀብ በመጋለጣቸው ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በተለያዩ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ጫናዎች ምክንያት ራሳቸውን የሚያጠፉ ዜጎች ቁጥር ቢጨምርም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ አሳዛኝ የሆኑ ራስን የማጥፋት ድርጊቶች ተበራክተዋል ተብሏል፡፡
ለአብነትም ከሰሞኑ ወላጆቹ በረሃብ የሞቱበት የ10 ዓመት የሰሜን ኮሪያ ህጻን ራሱን ከረሃብ ለማትረፍ ሲል የተመገባት አይጥ በመመረዟ ምክንያት ህይወቱ ማለፉ ብዙዎችን አሳዝኗል፡፡
ይህን ተከትሎ የረሀብ ጉዳይ ዋነኛ የሰሜን ኮሪያዊያን አጀንዳ ሆኗል የተባለ ሲሆን የፕሬዝዳንት ኪም ጆንግ ኡን መንግስት ብሄራዊ ራስን የማጥፋት መከላከል ግብረ ሀይል አቋቁመዋል ተብሏል፡፡
ይሁንና ረሃቡ እና ራስን የማጥፋት ድርጊት በኢኮኖሚ ጫና የመጣ በመሆኑ ግብረ ሀይሉ የተሳካ ስራ ላይሰራ እንደሚችል ተገልጿል፡፡
በአጠቃላይ በሰሜን ኮሪያ ራስን የማጥፋት ድርጊት በ40 በመቶ መጨመሩን የኮሪያ ደህንነት ሪፖርት ያስረዳል፡፡