በኢትዮጵያ በየዓመቱ 8 ሺ የሚደርሱ ሰዎች ራሳቸውን እንደሚያጠፉ አንድ ጥናት አመለከተ።
ራስን በራስ የማጥፋት ድርጊት የሥነ ልቦና ጫና ከማሳደሩም በላይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስን ያባብሳል፡፡
በጤና ሚኒስቴር የአዕምሮ ጤና ፕሮግራም ቡድን መሪ ዶክተር ደረጀ አሰፋ እንደሚሉት፣ በኢትዮጵያ ከአንድ ሚሊዮን ሰዎች ቢያንስ 80ዎቹ ራሳቸውን እንደሚያጠፉ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡
ይሄም፣ እንደ ዶክተር ደረጀ ገለጻ፣ ከቤተሰብ ባለፈ በማህበረሰቡ ላይም የስነ ልቦና ጫና እያሳደረ ይገኛል።
ራስን ለማጥፋት ከሚያነሳሱ ምክንያቶች ውስጥ በማህበራዊ ትስስር ላይ ያለ ክፍተት፣ በትዳር አለመጣመር፣ ትዳር መስርቶ ልጅ አለማግኘት፣ የወደዱትን ማጣት፣ ሰውን ለመጉዳት ራስ ላይ ርምጃ መውሰድ፣ የአካላዊ ጤንነት መጓደል፣ በአዕምሮ ስርዓት ውስጥ የኬሚካል ማነስ፣ ተጠቃሽ መሆናቸውን ዶክተር ደረጀ የማኅበራዊ ሳይንስ፣ የሥነ ልቡናና ሥነ ህይወት ልሂቃን አስተምህሮን በማጣቀስ ጠቁመዋል።
የአንዳንድ ጂን ሁኔታዎችም ራስን የማጥፋት ፍላጎት መነሻ ሊሆኑ እንደሚችሉ የዘረመል ጥናቶች ያሳያሉ፡፡
በዋናነት ራስን የማጥፋት ድርጊት ዕድሜያቸው ከ45 ዓመት በላይ በሆነ ወንዶችና ከ55 ዓመት በላይ በሆኑ ሴቶች እንደሚጨምር የሚናገሩት ዶክተር ደረጀ፣ በኢትዮጵያ ባህል ሁኔታው በሚፈጠርበት ወቅት የተለያዩ ማህበራዊ ቀውሶችን በመፍራት እንዲህ ዓይነት ሞት በግልጽ የሚነገር አለመሆኑን በማውሳት ቁጥሩ ከዚህም ከፍ ሊል እንደሚችል ተናግረዋል።
የአዕምሮ ህመም ራስን ለማጥፋት 95 በመቶ ያህል አስተዋፅኦ እንዳለውና ችግሩ ሥር ሳይሰድ በመለየት ሰዎች ህክምና እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በዓለም ላይ በዓመት 800 ሺ የሚሆኑ ሰዎች ራሳቸውን ያጠፋሉ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘገባ እንደሚያመለክተው፡፡
ምንጭ፡- ኢፕድ