በአሜሪካ ራስን የመግደል ወንጀል መጨመሩ ተገለጸ
ሀገሪቱ ራስን የማጥፋት ወንጀል ለመከላከል ድጋፍ የሚያደርግ ማዕከል ማቋቋሟን አስታውቃለች
በአሜሪካ የ11 ሰከንዱ አንድ አሜሪካዊ ራሱን እንደሚያጠፋ አዲስ ጥናት አመላክቷል
በአሜሪካ ራስን የመግደል ወንጀል (ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች ቁጥር) መጨመሩ ተገለጸ።
አሜሪካ እየጨመረ የመጣው ራስን የማጥፋት ወንጀል ለመከላከል ብሔራዊ ራስን የማጥፋት መከላከል ማዕከል አቋቁማለች።
ይህ ማዕከል ባዘጋጀው የአጭር የስልክ ጥሪ እና የጽሁፍ መልዕክት ዜጎች ራሳቸውን ለማጥፋት ሲያስቡ አልያም ራሳቸውን ለማጥፋት የሞከሩ ሰዎችን ካዩ የሚጠቁሙበት እና የስነ ልቦና ድጋፍ የሚያገኙበት ነው።
ይህ ማዕከል ከተቋቋመ የቆየ ቢሆንም ኮሮና ቫይሩስ መከሰቱን ተከትሎ አገልግሎት አቋርጦ ቆይቷል።
ካሳለፍነው ነሀሴ ጀምሮ ደግሞ ይህ ማዕከል ዳግም ወደ አገልግሎት የተመለሰ ሲሆን ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ብቻ ማዕከሉ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የራሴን ላጠፋ ነው መልዕክት መቀበሉ ተገልጿል።
በህዳር ወር ላይ ብቻ ከ154 ሺህ በላይ የራሴን ላጠፋ ነው መልዕክቶች እና ጥሪዎች ወደ ማዕከሉ መድረሳቸውን ዩኤስ ኒውስ ዘግቧል።
ከቀናት በፊት በተከበረው የ2023 አዲስ ዓመት ዋዜማ ላይ ብቻ 3 ሺህ 869 የእራሴን ላጠፋ ነው ጥሪዎች ወደ ማዕከሉ መላካቸው ተገልጿል።
ይህ ማዕከል ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ የ150 ሺህ ዜጎችን ህይወት ታድጓል የተባለ ሲሆን ራሳቸውን ለማጥፋት ለሞከሩ ዜጎች የስነ ልቦና እና ማማከር አገልግሎት መስጠት የማዕከሉ ዋና ተልዕኮ እንደሆነም ተገልጿል።
በአሜሪካ በተለይም ከ10 እስከ 34 ዓመት እድሜ ያሉት ሰዎች በአማካኝ በብዛት ራሳቸውን እንደሚያጠፉ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።